የዶሮ ሃብት ልማት የወጣቶችን ሕይወት እየቀየረ ነው።

3

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንቁላል ከልጅ እስከ አዋቂ የሚመገበው እና ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው ምግብ ነው። ለሰው ልጅ ጠቃሚ የኾኑ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል።

ይህ ጠቃሚ ምግብ በገበያ ላይም ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው እንቁላልን በማምረት በኩል በአማራ ክልል ምን ያህል እየተሠራበት ነው?

ይርጋ፣ አያሌው እና ጓደኞቻቸው የዶሮ እርባታ ሽርክና ማኅበር በደብረ ብርሃን ከተማ እንቁላል ምርት ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ይርጋ ወሰንየለህ ላለፉት አራት ዓመታት በዶሮ እርባታ እና እንቁላል ማምረት ላይ ተሰማርተው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ ከአረብ ሀገር ተመላሽ በኾኑ በስድስት አባላት የተመሠረተ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል የሥልጠና እና የመሥሪያ ቦታ እንደተመቻቸላቸውም ገልጸዋል፡፡ ለአምስት ሰዎች በቋሚ እና በሽያጭ ሥራ ለ13 ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩም ተናግረዋል።

የዶሮ እርባታ እና እንቁላል ማምረት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ እና ትርፋማ የሥራ መስክ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ አሁን ገበያ ላይ ያለው ዋጋ ለሥራው አዋጭ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ከ7 ሺህ ዶሮዎች በወር ከ200 ሺህ በላይ እንቁላል እንደሚያገኙ እና የገበያ ችግር እንደሌለባቸውም አንስተዋል፡

ያመረቱትን እንቁላል በከተማው፣ ለምሥራቅ አማራ አካባቢዎች እና ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ ገልጸዋል፡፡ በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ እስከ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ካፒታል እንደደረሰም ገልጸዋል፡፡ የዶሮ እርባታ ሥራ በጥንቃቄ እና በትኩረት ከተሠራ አዋጭ በመኾኑ ወጣቶች ቢገቡ ውጤታማ መኾን ይችላሉ ብለዋል፡፡

የብሩክ፣ አየለች እና ጓደኞቻቸው የዶሮ እርባታ ኅብረት ሽርክና ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ ብሩክ ግርማ በዘርፉ ለአምስት ዓመታት ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የማኀበሩ አባላት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተመረቁ ወጣቶች ናቸው።

የዶሮ እርባታ አዋጭ ዘርፍ ነው፤ በገበያ ላይም የእንቁላል ምርት በጣም ተፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በመንግሥት በኩል የቦታ አቅርቦት እና ተከታታይ የባለሙያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ገልጸዋል፡፡

በማኅበራቸው ከ1ሺህ 500 ዶሮዎች በወር ከ38 ሺህ በላይ እንቁላል እንደሚያመርቱ ተናግረዋል፡፡ ለአራት ሰዎች ቋሚ እና በእንቁላል ሽያጭ ከ20 በላይ ለሚኾኑ ሰዎች በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ከ200 ሺህ ብር ተነስተው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ካፒታል መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ታሪኳ እሸቱ የዶሮ እርባታ የከተማው ትልቅ አቅም ነው ብለዋል፡፡ የእንቁላል ምርት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ እና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ያለ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

እንደ ተቋም በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የሥልጠና፣ የቦታ አቅርቦት እና የሙያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው የተናገሩት፡፡ ዘርፉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ቁርጠኛ ኾኖ መሥራትን የሚጠይቅ ቢኾንም አዋጭ ሥራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ከተማው ለማዕከላዊ ገበያ ካለው ቅርበት አንጻር የገበያ ችግር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ በኢንተርፕራይዝ 340 እና በግለሰብ 1ሺህ 897 ዜጎች በእንቁላል ማምረት ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በጥቅል 2 ሺህ 237 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት፡፡ “የዶሮ ሃብት ልማት ለሥራ ዕድል ፈጠራም አቅም እየኾነ ነው” ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት 48 ነጥብ 7 ሚሊዮን እንቁላል ለገበያ መቅረቡን አስታውሰዋል። በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 11 ነጥብ 7 ሚሊዮን እንቁላል ተመርቷል ብለዋል።

የዶሮ እርባታ ሥራ አርቆ ማሰብን እና ትዕግስትን የሚጠይቅ፣ በርካታ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና ሃብት ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ በመኾኑ በተለይም ወጣቶች ቢሰማሩ ውጤታማ ይኾናሉ ነው ያሉት።

በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሳት እርባታ፣ ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ እንቁላል በክልሉ በሰፊው ይመረታል ብለዋል፡፡

እንደ ክልል ሰፊ የዶሮ ሃብት አለ፤ በቁጥር እስከ 23 ሚሊዮን ይደርሳል ነው ያሉት። 85 በመቶ የሚኾነው የአካባቢ ዝርያ ነው፤ 15 በመቶ ደግሞ የተሻሻለ ነው ብለዋል። አብዛኛው በክልሉ የሚመረተው እንቁላል የሚሰበሰበው ከአካባቢ ዝርያ መኾኑን ተናግረዋል።

በአረሶ አደሮች አያያዝ የአካባቢ ዝርያ ዶሮዎች በዓመት ከአንድ ዶሮ በአማካኝ እስከ 67 እንቁላል ይሰጣሉ፤ የተሻሻሉ ዝርያዎች ደግሞ እስከ 192 እንቁላል ይሰጣሉ ብለዋል። በተሟላ መንገድ ክትትል እየተደረገ የሚረቡ ዶሮዎች በዓመት እስከ 300 እንቁላል እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የዶሮ ሃብት ልማት አሠራር ተዘጋጅቶ ለሠለጠኑ ሴቶች ከ25 ዶሮ ጀምሮ እስከ 499 ይሰጣል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በከተማ አሥተዳደሮች 580 ሚሊዮን ብር በመመደብ በርካታ ሼዶችን እየተሠሩ ነው ብለዋል። በዞኖችም በሁሉም ወረዳዎች በእያንዳንዳቸው ቢያንስ ሦስት ሼዶችን ገንብተው ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት። በርካታ ወጣቶች ወደ ሥራ እንደገቡም ተናግረዋል።

በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን የተሻሻለ የአንድ ቀን ጫጩት ለአሳዳጊዎች ተሠራጭቷል። ከ45 ቀን ጀምሮ ለአርሶ አደሮች እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል። በክልሉ የዶሮ ብዜት ማዕከላት እንዲጠናከሩ እና ከሥራ ውጭ የኾኑትን ወደሥራ ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አዲስ የዶሮ ብዜት ማዕከል እና የመኖ ማቀነባበሪያ በሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮጀክት ተሠርቶ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ነው ያሉት።

እንደ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 16 ቢሊየን እንቁላል ተመርቶ ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ለማምረት ዕቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በዘርፉ ከ248 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየባሕር በር ጥያቄያችን የነበረንን እናግኝ ነው።
Next articleከ33ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ እንደሚያለማ የሰሜን ጎጃም ዞን ገለጸ።