
ደሴ፡ ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የ2ኛ ዙር የሴቶች የልማት ኅብረት አፈጻጸም ግምገማ እና የ3ኛ ዙር ምልመላን አስመልክቶ በደሴ ከተማ ምክክር አካሂዷል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሴቶችን በልማት ኅብረት በማደራጀት ረገድ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በተሠሩ ሥራዎች የዕቅዱን 51 በመቶ መፈጸም ስለመቻሉ ተመላክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር፣ የደቡብ ወሎ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊዎች በሰጡት አስተያየት ባለፈው በጀት ዓመት በአደረጃጀት ዘርፉ ሴቶች ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል፣ በጤና፣ በግብርና እና በትምህርት ዘርፎች ባከናወኗቸው ተግባራት ውጤታማ ኾነዋል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው ከሐምሌ 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በሁሉም ዞኖች 310 ቀበሌዎች ላይ በተሠሩ የአደረጃጀት ሥራዎች የዕቅዱን 72 በመቶ ማሳካት እንደቻሉም አንስተዋል።
በቀጣይ ከዞን እና ከወረዳ ባለፈ በ3ኛ ዙር ወደ ሞዴል መግባት የሚችሉ ቀበሌዎችን በመለየት ከእስካሁኑ የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት ወደ ተግባር ስለመገባቱም ገልጸዋል፡፡
በሴቶች ልማት አደረጃጀት ዘርፉ ከመጡ ለውጦች መካከል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በመልካም አሥተዳደር እና ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የልማት ኅብረቶቹ ሚና ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ፊኒክስ ሃየሎም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን