በምዕራብ ጎንደር ያለው ሃብት ከሀገር አልፎ አህጉርን መመገብ የሚያስችል ነው።

5

ጎንደር: ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በኢንቨስትመንት ዘርፉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በጎንደር ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው እያለሙ መኾናቸውን አንስተዋል። በሚገባ ተጠቃሚ ለመኾን የሚያስችል የብድር አቅርቦት እንዳልተመቻቸላቸውም ተናግረዋል።

በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት የአካባቢውን የመልማት አቅምን ያዳከመ መኾኑን ያነሱት ባለሃብቶቹ ሰላምን ለማምጣት ከመንግሥት ባሻገር ባለሃብቶችም አጋዥ መኾን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በመድረኩ ባለ ሃብቶች ከብድር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ላነሱት ቅሬታ መልስ የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጎንደር ዲስትሪክት የብድር ክፍል ኀላፊ ምሥጋናው ዘሪሁን ባንኩ አዳዲስ መመሪያዎችን በማዘጋጀት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች እገዛ ለማድረግ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።

የአካባቢው መሥተዳድር አካላት ባለሃብቶችን እና አርሶ አደሮችን የማደራጀት ሥራ በመሥራት ብድር እንዲመቻችላቸው ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል።

የኢትዮጰያ ልማት ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት ሥራ አሥኪያጅ እሱባለው ሰቦቃ የኢትዮጰያ ልማት ባንክ መረጃቸውን አጣርተው ለሚመጡ ባለሃብቶች ብድር እያመቻቸ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ዞኑ ለግብርና ሥራ የተመቸ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ እና ጥጥ ማምረት የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት ለቀጣናው ምርት መቀነስ ተጽዕኖ እየፈጠረ መኾኑንም አንስተዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የአካባቢን የመልማት አቅም ለማሳደግ በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት መመለስ ቀዳሚው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።

የሕዝቡ የመልማት ጥያቄ በሰላም እጦቱ ምክንያት እየተገታ መኾኑን ማኅበረሰቡ በተለያዩ ውይይቶች ላይ ያነሳል ያሉት ምክትል ኀላፊው ለሰላም መምጣት ባለሃብቶች እገዛ ማድረግ እንዳለባቸወም ተናግረዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ምዕራብ ጎንደር እና አካባቢው ለሀገር ዕድገት መሠረት የኾኑ ሃብቶችን አቅፎ የያዘ መኾኑን ተናግረዋል።

ምዕራብ ጎንደር እና አካባቢው የግብርና ምርት ከማምረት ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች፣ እጣን እና ሙጫን ጨምሮ ሌሎች ሃብቶች ያሉት መኾኑን ገልጸዋል። በአካባቢው ያለው ሃብት ከሀገር አልፎ አህጉርን መመገብ የሚያስችል መኾኑንም አስታውቀዋል።

አማራ ክልልን ለማልማት የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ማሳደግ ቀዳሚው ተግባር መኾኑን ያነሱት ኀላፊው የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኘውን የሰሊጥ ሃብት ጨምሮ ሌሎች የኢኮኖሚ አቅሞችን በሚገባ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል። መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የቀጣናው ባለሃብቶች የኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲያድግ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ባለሃብቶችን የሚያማርሩ ጉዳዮችን መፍታት የክልሉ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል።

የመልማት እና የመለወጥ ፍላጎቱ ከባለሃብቶች መታዘባቸውን የተናገሩት ኀላፊው የባለሙያ ድጋፍ ታክሎበት የዞኑን የመልማት አቅም ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አጭር የሕይወት ታሪክ