ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አጭር የሕይወት ታሪክ

11

አዲስ አበባ: ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በላቀ ምግባር፣ በጠለቀ ተግባር፣ በታመቀ ፍቅር፣ በእንግልት ማኅደር፣ በትግል መዘውር፣ የገዛ ነፍሥን በቁም ነጥቆ ለቸሩ ፈጣሪ፣ ለማኅበረሰብ እና ለሀገር መስዋዕት አድርጎ መባጀትም መዋጀትም የጥቂቶች የልዕልና እና የቅድስና መሰፈሪያ ነው።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የዚህ ወካይ፣ ከዚያም በላይ የሀገር ቀለም እና ልክ፣ የዘመናት መልክ፣ አድባረ ታሪክ፣ የትውልዶች ድልድይ፣ የዕውቀት እና የመልካም ጠባይ ሙዳይ፣ የደጋግ ሸሆች ብቃይ እና ቅጣይ፣ ሰብዓዊ ፀሐይ፣ በሁለንተና ሁሉን ዜጋ አገልጋይ፣ የሀገር ጥንታዊ ጥሪት፣ የሚጨበጥ ትውፊት፣ የሚዳሰስ ሀገረሰባዊ ድባብ እና ቅርስ፣ ቢጤ አልባ ሰብዓዊ ሀብት፣ ብርቅየ የወል ሕያው ወረት፣ አንጡራ ሊቀ ሊቃውንት፣ ኅብር የሃይማኖት የብሔር እና የፖለቲካ አስተሳሰብ የማይቃረናቸው የሀገር እናት የዜጎችም መጠለያ ማኅፀን ነበሩ።

እኝህ ድንቅ የዘመን ቡራኬ ስብዕና በአጋጠማቸው ህመም ምክንያት ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በ94 ዓመታቸው ጥቅምት 10/2018 ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከአባታቸው አቶ ኢድሪስ ዘለቀ እና ከእናታቸው ወይዘሮ መነን ሽፋው፣ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1924 በወሎ ቦረና ገነቴ አካባቢ ልዩ ስሙ “ዳሎታ” በተባለ መንደር ተወለዱ። ለአባት እና ለእናታቸው አራተኛ ልጅ ነበሩ። እናት እና አያታቸውን በልጅነት ተነጥቀው ነው ያደጉት።

በዕድገታቸው ወቅት የመንፈሳቸው ምሪት በቤተሰብ ስስት እና ሥነልቡናዊ ቅኝት ቢታጠርም፣ ወሰኑን ሰብረው እስከ ህልፈት ለተንጸባረቁበት የሕይዎት ዳና እራሳቸውን ሰጡ። ከምቾት አፀድ ወጥተው ከሥጋ ድካም ጋር የሚፀድቁበትን ዕጣፈንታ ገለጡ። እረኛም፣ ገበሬም፣ ነጋዴም ለመኾን የሞከረው ልጅነታቸው መጽደቂያ ፍኖቱ ግን ዕውቀት፣ ትምህርት እና ሥርዓት የነገሠበት አምባ ነበር። ይህም በብዙ ፈርጅ የሚገለጥ፣ የሚበየን፣ የሚሰነድ ቡቃያ አለው፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር “ገነቴ ዳሎታ” ከሼህ ከማል እሸቴ የቅዱስ ቁርኣን ከፊል ነቢብ ተማሩ። “ለገሂዳ” ከሼህ አሊ ገመች የቅዱስ ቁርኣን ነቢብ፣ የዓቂዳ (ሥነ መለኮት) ትምህርት ገበዩ። ወደ ዳሎታ ተመልሰው ከሼህ ከማል የሐነፊ ፊቕህ (ሥነ ሕግ) አገባደዱ። “ደላንታ” ወደ ሼህ አሊ አደም አቅንተው ቀሪ የፊቖህ ዕውቀት ሰነቁ። ወደ ዳሎታ ተመልሰው ከሼህ ዩሱፍ ተሰማ የፊቕህ (ሥነ ሕግ) ዝግጅት አጠናቀቁ።
በመቀጠል ወደ “ቦረና ውሻት” ሄደው በሼህ ጡሓ በጌምድሬ አማካኝነት የነሕው (የሰዋሰው) ትምህርት ጀመሩ።

ወደ “ከቶ” አምርተው በዐቢይ የዘርፉ መምህራቸው በሼህ ዐብዲል ሐሚድ በሽር አጠናቀቁ። ጉዟቸውን ሳያናጥቡ ወደ “ቦሩባ ገዳ” ተጉዘው በሼህ የሕያ ሰዒድ አማካኝነት የቅዱስ ቁርኣን ተፍሢር (አንድምታ) ገበዩ።

በመጨረሻም በደሴ እና በአዲስ አበባ ከተማዎች ከሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ዘንድ የሐዲስ፣ የመንጢቅ፣ የበላጛ፣ የዓሩድ፣ የበዲዕ፣ የእስቲዓራ፣ የመዓኒ፣ የሒከም የትምህርት ዘርፎችን ቀሰሙ።

በዚህ ሂደት አዕምሯቸውን እና ልቡናቸውን ከአለመለሙ በኋላ መንፈሣዊ ቁመናቸውን ወደ ማነጽ ተሸጋገሩ።

ከሼህ ሐሰን ፈቃዱ የተለያዩ ዕለታዊ ዊርድ (መዘክር) አገኙ። እንደ አብራሔ በሚቆጥሯቸው እና በዘጠነኛው የኢትዮጵያ ዓሊሞች (ሊቀ ሊቃውንት) የበላይ ጠባቂ በሣልሣዊ ዳንይ (ሼህ ሙሐመድ ዘይን) በኩልም የአዝካር፣ የኸልዋ ጽሞና እና ተመስጥኦ ሙሉ ፈቃድ ወረሱ።

በሼህ አሕመድ ኑር (አበል ጀማል) ጅማ አማካኝነት ቋሚ ተጨማሪ የዚክር ወረት የማካተት ዕድል አገኙ። በሼህ ሙሐመድ ኮሬብ እንዲሁም በየመናዊው በሼህ ሰይድ አሕመድ ዓሊ የመኒ አማካኝነት መንፈሣዊ እና መለኮታዊ ቅዱስ ንባቦችን ለመከወን የሚያስችል ችሮታም አገኙ።

ይህም ሂደት በ13 መምህራን ድጋፍ በ35 ተከታታይ ዓመታት እና የሙሉ ጊዜ ጥረት ተጠናቀቀ።

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ “መምህር (ሙደሪስ ሙዓሊም)” የኾኑት ገና በተማሪነታቸው (በደረስነታቸው) ወቅት ነው፡፡ ምንም እንኳን ምቾት እና ተድላ ያልነበረ ቢኾንም የእረፍት፣ የቤተሰብ ዚያራ፣ የግል የትምህርት ክትትል ትኩረታቸውን ቀንሰው ለእኩዮቻቸው እና ለበታቾቻቸው ያወቁትን ያካፍሉ ነበር፡፡ በዳሎታ፣ በደላንታ፣ በከቶ የዕውቀት ማዕከላት የከፍተኛ ደረሳ ማዕረግ አግኝተው በርካታ ዓሊሞችን ማስተማር ችለዋል፡፡

በዕውቀት መምህሮቻቸው ተገምግመው ተመጣጣኝ የመምህርነት ቁመና ሲያገኙም በ1958፣ በ1959፣ በ1960 ከሦስት መምህሮቻቸው “የመምህርነት ፈቃድ (ኢጃዛ) አገኙ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1960 ጀምሮ እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም ድረስ – በአንዋር እና በኑር መስጅዶች፣ በበኬ እና በሰፈራ አካባቢ ባቋቋሟቸው የዕውቀት ማዕከላት እልፍ አዕላፍ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የሚጎርፉ ዕውቀት ፈላጊዎችን ያስተምሩ እና ለመምህርነት አብቅተውም ያሰማሩ ነበር፡፡

ይህንን ሲያደርጉ ከየትኛውም አካል ደመወዝ ሳይጠይቁ በተለይም ኑሯቸውን ማደላደል ከቻሉበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ የደረሳዎችን መሠረታዊ ፍላጎት እራሳቸው እያሟሉ ያገለግሉ እና ትውልድን ያለሙ ነበር፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር የዕውቀት፣ የሃይማኖት እና የማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመመሥረት ሂደት የላቀ ተሳትፎ አላቸው፡፡ በ15 ዓመታቸው መስጅድ፣ ኸልዋ፣ የሸኻቸውን የመኖሪያ ቤት ብቻቸውን በግል ጉልበት እና ግብዓት መመሥረት ችለዋል፡፡

ከዚያም ወዲህ እስከ ኅልፈታቸው ወቅት በአዲስ አበባ ዘጠኝ መስጅዶችን፣ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል በመቶዎች የሚቆጠሩ በርካታ የዕውቀት እና የአምልኮ ተቋማትን በቀጥታ እና በሙሉ ድጋፍ እንዲሁም በማስተባበር መሥርተዋል፡፡

በ1967 የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጠቅላይ ምክር ቤት ሲቋቋም ከቀዳሚ አባላት መካከል በመኾን በተቋም ግምባታው ሂደት እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ደማቅ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡

ለተቋሙ ሕጋዊ ተክለ ሰውነት በማጎናጸፍ ጥረት ውስጥም የጎላ ስኬት አስመዝግበዋል፡፡ የኢስላማዊ ባንክ፣ ሚዲያዎች እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲመሠረቱ ብሎም እንዲስፋፉ በማበረታታት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር በደረሳነታቸው ወቅት በተለያዩ የዕውቀት ማዕከላት ለረዥም ጊዜያት “አሞጣይ” (አስጠኝ) ኾነው ደረሳዎችን እና የዕውቀት ማዕከላትን መርተዋል፡፡ አስተዳድረዋል፡፡ በ1959 ወደ አዲስ አበባ ከአቀኑበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከ1960 ጀምሮ በኑር መስጅድ ለ16 ዓመታት በምክትልነት እና ለ3 ዓመታት በዋና ኢማምነት፤ በ1967 የቀዳሚው የእስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት መሥራች አባል፤ የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች ጉባኤ ሠብሣቢ፤ የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች የፈትዋ ኮሚቴ መሥራች እና አባል፤ የሀገር አቀፍ የዑለማ ጉባኤ ሠብሣቢ እና ሙፍቲ የነበሩ ሲኾን በዚሁ ወቅት በ11 ዓመታት ውስጥ በ58 የኢትዮጵያ ከተሞች ተዟዙረው በሙስሊሞች መካከል እንዲሁም በሙስሊሞች እና በሌሎች ወገኖች መካከል ከ130 በላይ ለቅራኔ እና ለግጭት የጋበዙ አጀንዳዎችን እልባት መስጠት ችለዋል፡፡

የአዲስአበባ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ሠብሣቢ እና ለዘጠኝ ዓመታት ዋና ሠብሣቢ፤ የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጂ እና ዑምራ ዘርፍ እንዲሁም የዳዕዋ እና የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ፤ በ2010 ዓ.ም በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ዋና ሠብሣቢ፣ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት፤ ከ1960 ዓ.ም እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መስጅዶች በመምህርነት፣ በሥነ ምግባር ማነጽ እና በመካሪነት አገልግለዋል፡፡

በሌላ በኩል በብሔራዊ የሰላም፣ የዕርቅ፣ የሽምግልና፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴዎች እና ቡድኖች አባል እና አስተባባሪ በመኾን ያገለገሉበት አጋጣሚም ሰፊ ነው፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር በደረሳነት ዘመናቸው በድምሩ ከ370 በላይ ድርሳናትን በእጃቸው ገልብጠው ጽፈዋል፡፡ ከ80 በላይ የዓረብኛ እና የዓጀም የግጥም መድብሎችን አዘጋጅተዋል፡፡ እንዲሁም ለሕትመት ያልበቁ፦ የኢትዮጵያ ዓሊሞች ዝክረ ታሪክ (በዓረብኛ)፣ የእራሳቸው ግለ ታሪክ (በዓረብኛ)፣ ሰባት የአማርኛ ትርጉም መጻሕፍትን፣ የቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ሰፊ ማብራሪያ እና ትንታኔ አዘጋጅተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የቅዱስ ቁርኣን ትንታኔን ጨምሮ ሌሎች የእነጻ መሰናዶዎች ከ360 በሚበልጡ ሲዲዎች እንዲሰነድ አስችለዋል፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንደ ገለልተኛ ፀሐይ አንጸባራቂ የሕይዎት መርሆች ነበሯቸው፡፡ “ሰውነት ይቀድማል”፣ “ፈጣሪን አናሞኘው የልባችንን ይመለከታል”፣ “እንስሳ አምሳያውን በማይጎዳበት ሥነ ተፈጥሮ ሰው ሰውን እንዴት ይጎዳል?”፣ “የሀገር ችግር በጥሩ መሪ በጥሩ ተመሪ ይቀረፋል”፣ “ሰውን የሚጠቅመው ወይም የሚጎዳው ዘሩ ሳይኾን ሥራው ነው”፣ “አንድነት ይበጃል መተባበር ይጠቅማል”፣ “ሳይርበን አንበላም፣ ስንበላም እስክንጠግብ አንመገብም” የሚሉ እና በቀላሉ ዕዝነ ሕሊናን ዘልቀው፣ ሰርነ ልቡናን ጥሰው የሚቆጣጠሩ የሕይዎት መርህ ነበሯቸው፡፡ ሠርቶ በማብላት፣ ጠንክሮ በመሥራት፣ አግኝቶ በማካፈል እና ለሌሎች በመኖር ተግባራቸውም ሕያው ተምሳሌት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን ከአንደበታቸው ሳይዘነጉ፣ ከዱዓቸው ሳያጎድሉ፣ የእንባ ዘለላቸውን ሳይከትሩ ለሀገር ታምነው፣ በሀገር ፍቅር ተሸምነው ኑረዋል፡፡ በዓድዋ የተሰው አጎታቸውን አርበኛ ፋርስ ቱፋን በክብር ኩራት ከማመሥገን ጀምሮ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጻዊያን አቻ ሊቀ ሊቃውንት ጋር በአደባባይ እስከመሟገት የሚወሳ ተጨባጭ በረከት አላቸው፡፡

በአስቸጋሪ ወቅቶች ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚበጅ አቅጣጫ በመስጠት፣ መንፈሳዊ ግሳጼ እና ለበጎ ሥራ ቡራኬ በመለገስ ለሀገር ሽግግር እንዲሁም መረጋጋት ንጹህ ድርሻ አላቸው። ለሀገር ልማት፣ ለውጥ እና ዕድገት ሁለንተናቸውን ተባባሪ የማድረጋቸውም ምስጢር የሀገር ፍቅር ነው።

ከ12 በሚበልጡ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የምዕራቡ ዓለም ሀገራት በተዟዟሩበት ወቅትም ሀገራቸውን እና ባሕላቸውን የሚያፈነጥቅ መልዕክት እና አለባበስ ከማቅረብም ተቆጥበው አያውቁም ነበር፡፡ አዲሱ ትውልድ ሀገሩን እንዲያፈቅር፣ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ እንዲተባበር ከመምከር የታቀቡበት ጊዜ አልነበረም።

በቀደምት ሊቀ ሊቃውንት ከፍተኛ ማዕረግ እና ምስክርነት ያገኙት፣ ለአስርት ዓመታት ባበረከቱት ነጻ ሁለንተናዊ ግልጋሎት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲሁም ሃይማኖተኛ እና ፖለቲከኛ ዘንድ አንጸባራቂ ልባዊ ምሥጋና የተጎናጸፉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በ1966 በመሠረቱት ትዳር ዘጠኝ ልጆችን ያፈሩ ሲኾን እልፍ አዕላፍ ዓሊሞችን እና ደረሳዎችን እንዲሁም የዕውቀት ማዕከላትን መተካት ችለዋል፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በእግራቸው ተጉዘው ያከናዎኑትን ጨምሮ 40 ጊዜ የሐጂ ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፡፡ እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም ድረስ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ መንፈሳዊ ንቃታቸው እጅግም የተሟላ ነበር፡፡

ከሳምንቶች በፊት በአጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም አርፈዋል፡፡ አሏህ የጀነት ያድርጋቸው። ሕዝበ ሙስሊሙም አርዓያዊ ትውፊታቸውን ያስቀጥል። የሀገር መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ሙፍቲ እና መሰሎቻቸው የደከሙለትን ሰው ተኮር እሴት የዘወትር መመሪያ አድርገው መንፈሳዊ መሪያቸውን ያስታውሱ።

ለሀገር ሰላም እና ዕድገት የመንፈሳዊ መሪዎች አርዓያነት ይቀጥል። ሰላምና ፍቅር ለሁሉም ይስፈን።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ማስተዋልን፣ ትዕግስትን፣ ካስማቸው እና ድንኳናቸው አድርገው የኖሩ እንቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next articleበምዕራብ ጎንደር ያለው ሃብት ከሀገር አልፎ አህጉርን መመገብ የሚያስችል ነው።