
ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስከሬን የሽኝት ሥነ ሥርዓት በሚሊኒየም አደራሽ እየተካሄደ ነው።
በሽኝት ሥር ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮጵያ ዛሬ ታላቅ ሰው አጥታለች፤ መሪር የሀዘን ቀን ነው ብለዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ “በሕይወት ዘመናቸው ማስተዋልን፣ ትዕግስትን፣ ካስማቸው እና ድንኳናቸው አድርገው የኖሩ እንቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለዋል። ለመላው ኢትዮጵያዊ ይህንን ዕውቀት ያስተማሩ መኾናቸውንም ነው ያሉት።
በዕውቀታቸው፣ በጥበባቸው እና በእርጋታቸቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ማሰላሰልን፣ ማጤንን እና አቅል ማድረግን ማስተማራቸውንም ገልጸዋል።
ደግ አባት፣ ቅን መምህር ነበሩ ነው ያሉት። በዕውቀት ልግስናቸው፣ በመልካም አበርክቷቸው ምንጊዜም ሲታወሱ የሚኖሩ አባት ናቸው ብለዋል። ምንኛ ዕድለኛ ናቸው? ምን አይነትስ ተሰጥኦ እና መልካምነት ነው? ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ በሁላችንም ውስጥ ሲዘከር እና ሲታወስ የሚኖር እንደኾነም ገልጸዋል።
የአምላክ ነህና እውን ወደ አምላክ ትመለሳለህ ይላል አስተምህሮቱ፣ ትምህርቱ ይህም ቢኾን አባታችን ለእኛ ግን ጎድሎብናል ነው ያሉት። የማይቀር ቢኾንም ጉድለቱ ግልጽ ነው ብለዋል።
ጥበብዎን፣ አስተውሎትዎን፣ ጸጋዎን አጣነው፤ እውን ምን ያክል ትዕግሥት ተላብሰው ኖረዋል? አርቆ አሳቢነትዎ ምን ያክል ጥልቅ ነበር? መልካምነት እና ጸጋውን አጥተናል ነው ያሉት።
የእርስዎ ሃሳብ፣ መልካምነት፣ በጎነት፣ አርቆ አስታዋይነት፣ ቻይነት፣ አስታራቂነት፣ ሰው መኾን የሚጠናው እኛ መልካም አርዓያነትዎን ስንከተል ብቻ ነው ብለዋል።
እርስዎ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነዎት ብለዋቸዋል። ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መጽናናትንም ተመኝተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን