“ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አብሮነትን እና ሰላምን የሚሹ፣ ለሰላም የተጉ አባት ናቸው” ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

9

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስከሬን የሽኝት ሥነ ሥርዓት በሚሊኒየም አደራሽ እየተካሄደ ነው።

በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የእሳቸው ሕልፈት ለሕዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገር ትልቅ ጉድለት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔን በላይነት የመሩ እና ለሰላምና ለአንድነት የሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ሁልጊዜም ሰላምን የሚያስቀድሙ፣ ከሁሉም ነገር በላይ ሰውነትን የሚያስቀድሙ፣ ሰውነት ከሁሉ በላይ ነው የሚሉ፣ አብሮነትን እና ሰላምን የሚሹ፣ ለሰላም የተጉ አባት ናቸው ብለዋል።

በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ እና ክብርን የተጎናጸፉ የሀገር አባት፣ የሀገር ዋርካ መኾናቸውን ተናግረዋል። የእሳቸው ምክሮች እና ተግሳጾች እንደሚሰሙም ገልጸዋል።

ደጋግመው “ሰውነት ከሁሉም በላይ ነው” የሚለው ንግግራቸው ዘመን ተሻጋሪ መኾኑን አንስተዋል። ከህልፈታቸውም በኋላ የሚታወሱበት ድንቅ ንግግር መኾኑን ገልጸዋል።

ከእርሳቸው ብዙ ጥበብ ማስተዋላቸውንም አንስተዋል። በመምህርነታቸው፣ በመሪነታቸው፣ በአባትነታቸው እና ለሀገር ባደረጉት አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንደሰጣቸውም አስታውሰዋል።

እርሳቸው የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባት መኾናቸውን ገልጸዋል። እርሳቸው ዛሬ ቢያልፉም ሥራቸው ከእኛ ጋር ይኖራል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሰውነትን ያስቀደሙ፤ ለሀገር ሰላም የደከሙ”
Next article“ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ማስተዋልን፣ ትዕግስትን፣ ካስማቸው እና ድንኳናቸው አድርገው የኖሩ እንቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ