
ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰውነትን አስቀድመዋል፤ በአንደበታቸው ሰላምን ሰብከዋል፤ በአኗኗራቸው ፍቅርን አስተምረዋል፤ ስለ አንድነት፤ ስለ አብሮ መኖር ያለ መታከት ታትረዋል።
ባማረ ጥርሳቸው ፈገግ ሲሉ ሀገር የሳቀች ትመስላለች፤ ፈገግታቸው ሲጠፋ ሀገር እንዳዘነች ትቆጠራለች፤ በዘመናቸው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን አስቀድመዋል፤ አንድነት እና አብሮነትን ለትውልድ ሁሉ ነግረዋል።
ሰው ሁኑ! እያሉ ትውልዱን ገስጸዋል፤ ጥልና ጥላቻን ተጸይፈዋል፤ ዘረኝነትን ጠልተዋል፤ ቂም እና በቀልን ነቅፈዋል። መለያየትን አውግዘዋል። ከሁሉም ሰውነት ይቀድማል እያሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ተናግረዋል፤ ሁሉም ከሰውነት በኋላ ይከተላል፤ ሁሉም ከሰውነት በኋላ ይመጣል፤ ሰውነት ከሌለ ሁሉም ይቀራል፤ ሁሉም እንዳልነበር ይኾናል እያሉ በቀናች ልባቸው አስተምረዋል፤ ትውልድ ኾይ ሰውነትን አስቀድም እያሉ ለዓመታት ድምጻቸውን አሰምተዋል። ሰውነትን አስቀድሙ እያሉ፤ በአንደበታቸው ሰላምን እያስተማሩ ወደ ወዲያኛው ዓለም አልፈዋል።
እርሳቸውን ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት አባታችን ይሏቸዋል፤ የሀገር አባት፣ የሀገር ዋርካ እያሉ ያወድሷቸዋል፤ ያለ ልዩነት የሁሉ አባት ናቸው እና ያለ ልዩነት ልጆቻቸው ይወዷቸዋል ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ።
እርሳቸው ዋርካ ናቸው ሰላም የናፈቀው ትውልድ ሁሉ የሚያርፍባቸው፤ እርሳቸው የፍቅር ምሳሌ ናቸው ፍቅርን የማያውቅ ፍቅርን የሚማርባቸው፤ እርሳቸው የአንድነት አብነት ናቸው አንድነት የሚቀሰምባቸው፤ እርሳቸው የሰውነት ልክ ናቸው ሰውነት የተገለጠባቸው፤ እርሳቸው እውነተኛ ሽማግሌ ናቸው እርቅ የሚጸናባቸው፤ እርሳቸው እውነተኛ አባት ናቸው ልጅ ሁሉ የሚረጋጋባቸው።
ሃይማኖታዊ አኗኗርን ኖረዋል፤ አላህ የሚወደውን ፈጽመዋል፤ በአንደበታቸው መልካሙን ነገር ተናግረዋል፤ በአኗኗራቸው ሃይማኖትን ገልጸዋል፤ የፈጣሪ ትዕዛዛትን አክብረዋል፤ የተወደደውን ሁሉ አድርገዋል። ደገኛ አባት፤ ቅን መምህር፤ መጠጊያ ዋርካ፤ መጠለያ ዋሻ፤ የፍቅር ሰው ነበሩ።
በዘመናቸው እንፈቃቀር፣ እንዋደድ፣ እንረዳዳ፣ እንተባበር፣ የበታቹ የበላዩን ያክብር፣ የበላዩ ለበታቹ ይዘን እያሉ የኖሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የተወለዱት በወሎ ክፍለ ሀገር ገነቴ እንደኾነ ይነገራል።
እኔ የተወለድኩበት እና የመሻይኮቹ ቤት በአሻገር ነበር። ወደዚያ ሄጄ ቁርኣን መቅራት ጀመርኩ። ለውህ የሚባል ከእንጨት የተጠረበ ቁርኣን የሚጻፍበት ነበር ። ያን ይዤ ከብት እያገድኩ ቁርኣን ቀራሁ ይላሉ። ቁራን እየቀሩ ለወላጆቻቸው አርሰዋል፤ አርመዋል፤ አጭደዋል፤ ነግደዋል። ዋናው ሥራየ ግን ግብርና ነበር። አባቴም ገበሬ ነበርና ይላሉ።
ለወላጆቻቸው እያገለገሉ በሌሊት ወደ መስጊድ እያቀኑ ከወሎ መሻይኮች ዘንድ በጥበብ እና በማስተዋል በጥበብ ተማሩ። ቁርኣን ስቀራ አንጥፌ ተኝቼ አላውቅም፤ እራት እና ምሳም ትኩረት ሰጥቸ በልቼ አላውቅም ጥቂት እየበላሁ፣ እንቅልፍንም ትቼ በትምህርት በረታሁ እንጂ። ከመሻይኮች እየተማርኩ፣ በጎን ደግሞ አስተምራለሁ ነው የሚሉት።
እርሳቸው ለዓመታት ለሀገራቸው እና ለሃይማኖታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ኖረዋል። እርሳቸው የሰውን መጎዳት አይሹም፤ ለማንም ቢኾን ክፉ ነገርን አይመኙም። ክፉን በመልካም የሚመልሱ፤ የተቆጣን የሚያበርዱ ናቸው ይሏቸዋል።
አያሌ ተማሪዎችን አፍርተዋል። አንድነት ለሀገር፣ አንድነት ለሕዝብ ጠቃሚ ነው እያሉ ሲያስተምሩ ነው የኖሩት። እርሳቸው በኢትዮጵያ አውራጃዎች እየተመላለሱ ሃይማኖትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን አስተምረዋል። ከኢትዮጵያ አልፈው በሌሎች ሀገራትም ሃይማኖትን እና ሰላምን ሰብከዋል።
በርከት ያሉ ኪታቦችን ደርሰዋል፤ ከአረብኛ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል። ሰዎች ተጣልተው ጥዬ አልሄድም፤ አፉ አባብዬ፣ አሳትርቄ እሄዳለሁ እንጂ ይላሉ። እኔ ሰውን አልመርጥም። እኔ ዘንድ ሰው ሁሉ እኩል ነው። ለሁሉም አዝናለሁ፤ ለሁሉም አለቅሳለሁ። እኔ ስናገር ሰው እንዲወደኝ ብዬ አይደለም፤ ይልቅስ ለሕዝብ እና ለሀገር የሚጠቅመውን እናገራለሁ እንጂ ነው የሚሉት።
ማንም ሰው ፈጣሪውን ከፈራ፣ ለሰው ካዘነ ይፈራል፤ ይከብራል። እኔ ለአንድነት አንድ ዓመት አይደለም ያለቀስኩት ረጅም ዓመታት እንጂ ይላሉ።
የእርሳቸው ተማሪዎች አንደኛውን ለማስደሰት ብለው ሌላኛውን አይጎዱም፤ ሰው ባለው ነገር ሳይኾን በሰውነቱ ነው መለካት ያለበት ይላሉ ይሏቸዋል። የትኛውም ሰው ቢኾን ሲያናግራቸው ጀሯቸውን አዝንብለው ይሰማሉ፤ በቅን ልቡናም ያደምጣሉ፤ የተገባውን መልስም ይሰጣሉ ነው የሚሏቸው።
ሀገሬን እወዳለሁ። ሀገሬን ባልወድ ኖሮ በውጭ ሀገራት እንድኖር ተለምኜ ነበር። ግን የውጩን አልፈለኩትም። ሀገሬን ሳይ ብሞት እንኳን በመሬቷ ሳርፍ አሏህ የሚቀጣኝ አይመስለኝም ይላሉ። እርሳቸው ሀገራቸውን እስከዚህ ድረስ ነው የሚወዱት። ለማስመሰልም አይደለም። ለይሉኝታም አይደለም። ከልብ ከአንጀት ነው እንጂ።
ኢትዮጵያ መልካም ፀባይ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት ናት። እኔ ስኖር ቤተክርስቲያን ሢሠራ ሙስሊሙ እያገዘ፤ መስጊድም ሢሠራ ክርስቲያኑ እያገዘ፤ እስላም እና ክርስቲያን በአንድ ዳስ እየተሞሸረ ነው። ይህች ናት ኢትዮጵያ። ይሄን የቆዬ መልካም ነገር ያበላሸብን ፖለቲካ ነው። የሀገራችን ሕዝብ በጣም ንጹሕ ሕዝብ ነው። የበላዩን እና መሪውን የሚያከብር ነው ይላሉ።
የፊተኞቹ ሰዎች የኢትዮጵያን ሰው መልካም ነገር አስተምረውት አልፈዋል፤ አሁን ፈተና የገጠመው ይህ ነው፤ ሕዝባችን የተሳሳረ ነው፤ ተወዳጅ ነው፤ አሁን ነው መርዝ የተነሰነሰበት፤ ይህን መርዝ ለማጥፋት ደግሞ መተባበር አለብን፤ ግን በአንድ ዓመት አይለቅም፤ ልፋት ይጠይቃል፤ ግን መልቀቁ አይቀርም ነው የሚሉት።
እኔ ለሀገሬ አለቅሳለሁ፤ አልተኛም፤ የእኛ ሕይዎት እኮ የተወሰነ ነው፤ ሁልጊዜ የሚኖር የለም፤ ሲሞትም ታሪኩ ማማር አለበት። መጥፎ የሠራ ሰው ከሞትም በኋላ ይጠላል ይላሉ። ይሄን ሲናገሩም እያለቀሱ ነበር። የሚናገሩት ሁሉ ከአንጀታቸው እና ከልባቸው እንደኾነ እንባቸው ይመሰክራል።
ሃይማኖት ልባዊ መኾን አለበት፤ አስተማሪው ፈጣሪውን የሚፈራ በኾነ ጊዜ ተከታዩ ጠንካራ ይኾናል፤ የሚሰጣቸው ዕውቀት ከልብ ስለኾነ ይሰሙታል ይላሉ። ሰውን እንዲያከብር፤ የበላዩን እንዳይዘልፍ፣ የበታቹንም እንዳይንቅ የሚያደርግ ትምህርትም አለ፤ ይህን የተማረ ሰው ያከብራል። ሰውን በብዙ የሚያስተካክለው ዱዓ ነው፤ ዱዓ ሲደረግ ሀገር ሰላም ትኾናለች፤ ሕዝብም ተዋዶ በሰላም ይኖራል፤ አሏህን የሚፈራ ለሀገር እና ለሕዝብ ይጠቅማል ነው የሚሉት።
እኔ ለትውልዱ የማስተላልፈው ከሀጥያት እንቆጠብ፣ ሰውን አንመቅኝ፣ ሰው ከሰው ጋር ይተዛዘን፤ ሀገራዊ አመለካከት ይኖረን፤ ሕይዎት የተወሰነ ነው። ሥልጣን እርባና የለውም ኀላፊ ነው። ዋናው ነገር ሀገር ነው ይላሉ።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ከልጅነት እስከ ሕልፈት ድረስ ለሀገራቸው መልካም ነገርን አድርገዋል፤ እውነተኛ የሃይማኖት አባት ኾነው ስለ እውነት ኖረዋል።
ለሀገራቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ የተሰጣቸው እኒህ ታላቅ ሰው በትውልድ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። በክፉ ዘመን የተገኙ ደገኛ አባት ናቸውና ከሞትም በኋላ ምግባራቸው እየተነሳ ይወደሳሉ። ይታወሳሉ።
እኒያ ታላቅ ዋርካ ያለ ስስት ሀገራቸውን አገልግለው፤ ወደሚወዱት ፈጣሪ ዘንድ ሄደዋል። ብዙዎችም ሃዘናቸውን እየገለጹ ነው። የብዙዎች የሃዘን አገላለጽ ልብ ይነካል። ሀገር እና ሕዝብ ያጣቸው ታላቅ አባት ናቸውና የሕዝብ የሀዘን አገላለጽም የእርሳቸውን ታላቅነት እና ደግ አባትነት ይገልጻል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ
“አቤቱ፥ አድነኝ፥ ደግ ሰው አልቋልና” ብለው በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን አንስተው “እግዚአብሔር በየዘመናቱ ሀገርን ያለ መካሪ፣ ሕዝብን ያለዘካሪ አይተወውም፤ ለዚህም ምስክሩ ታላቅ አረጋዊ፣ የበሳል አዕምሮ ባለቤት፣ ሀገርን የሚወዱ፣ ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፣ የተጠቁት ወዳጅ ፣ የትውልድ አባት የኾኑት የክብር ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ነበሩ” ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በጣት ከሚቆጠሩ አረጋውያን፣ አፈ ማር ከኾኑ መካሪዎችዋ መካከል አንዱ የኾኑትን፣ ለመወደድ የታደሉትን የዘመናችን ጌጥ አጥታለች፡፡
ይህንን የድካም ዓለም መገላገል ለእርሳቸው ዕረፍት ቢኾንም ለሀገር ግን ታላቅ ጉዳት ከመኾኑም በላይ ዕድሜን ከጥበብ ጋር ያዋሐዱ በሁሉም ዘመን አይገኙምና ሀዘናችን ጥልቅ ነው” ብለዋል ቅዱስነታቸው።
እኒህ አረጋዊ አባት በሁሉም ዘንድ የተወደዱ ናቸውና በሀዘናቸው ሁሉም ተከፍቷል። ከልብም አዝኗል። ዛሬ መጠጊያ ዋርካው ወድቀዋል፤ የሁሉም አባት አልፈዋል። ነገር ግን አበው እንዳሉት ” ወድቆ የማይሰበር፣ ሞቶ የማይቀበር” ከፍ ያለ ስም አላቸውና ሁልጊዜም ስማቸው ከመቃብር በላይ ይኖራል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!