የአሜሪካ ዶላር ቅቡልነት ማክተሚያ እየተቃረበ መሆኑን ብሎምበርግ ዘገበ፡፡

311

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) ለ60 ዓመታት የአብዛኞቹ ሀገራት የመጠባበቂያ የባንክ ክምችት መለኪያ ሆኖ የዘለቀው የአሜሪካ ዶላር ቅቡልነት እያከተመ እንደሆነ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡ የአሜሪካውያን የኑሮ ሁኔታ ለዓለም ሚዛን ሆኖ መቆየቱ የዶላርን ቅቡልነት ማስቀጠሉን ያመለከተው ዘገባው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተደቆሰው የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የኑሮ ሚዛንነቷን ማሳጣቱን ገልጧል፡፡

ከአሜሪካ ምጣኔ ሀብት መዳከም በተጨማሪ ሀገሪቱ እንደ ልዩ አድራጊ ፈጣሪ የመቆጠሯ ጉዳይም አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ብሉምበርግ አመላክቷል፡፡ የሀገራት ውስጣዊ የምጣኔ ሀብት መሠረትና በውጭ ሀገራት የአሜሪካ የጥንካሬና ድክመት ሁኔታ ምዘና የዶላርን ቅቡልነት ማብቂያ የሚያመለክቱ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተፅዕኖ አስቀድሞም የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት ማሽቆልቆል እንደጀመረ ያስታወሰው ዘገባው በዚህ የአውሮፓውያን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሀገራዊ የቁጠባ መጠን 1 ነጥብ 4 ከመቶ እንደነበርና ይህም በሀገሪቱ ታሪክ 5ኛው ዝቅተኛ የቁጠባ መጠን የተመዘገበበት እንደሆነ አብራርቷል፡፡

የሀገራት ባንኮች በዶላር መጠባበቂያ ገንዘባቸውን ስለሚያስቀምጡ ግን ሳያውቁት አሜሪካን ይደጉማሉ፤ በዚህም በቂ ቁጠባ ከውጭ ታገኛለች፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ስበቷ ግን ከ1982 (እ.አ.አ) ጀምሮ እየቀነሰ እንደሆነ ነው የተመላከተው፡፡

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የቁጠባ መውረድ ከኮሮናቫይረስ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ጋር ተዳምረው የአሜሪካን ዶላር የበላይነት እንደቀነሱት ታውቋል፡፡ የዚህ ዓመት የበጀት ጉድለት እስከ 19 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚሆንም ተገምቷል፤ በእርግጥ በቀጣዩ የአውሮፓውያን በጀት ዓመት ወደ 9 ነጥብ 8 በመቶ እንደሚወርድ ተስፋ ተደርጓል፡፡

Image may contain: 2 people

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሚሊዮኖች ሥራ ማጣታቸው ደግሞ የበለጠ የበጀት ጉድለት መንስኤ እንደሚሆን ተመላክቷል፤ የሥራ ማጣቱ የቁጠባ መጠንን በእጅጉ ይቀንሰዋልና፡፡ የቁጠባ መጠን በሂደት ከዜሮ በታች 10 ሊደርስ እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡ ይህ ደግሞ በአሜሪካ የምጣኔ ሀብት ታሪክ ታይቶ የማያውቅ አደጋ ያስከትላል፡፡

በዚህም ቀውስ ውስጥ ሆኖ የአሜሪካ ዶላር በጥር ከነበረበት የመግዛት አቅም ሚያዝያ ላይ ሰባት ከመቶ ጨምሮ መገኘቱን ያመለከተው መረጃው ዕድገቱ ግን በሌሎች ሀገራት ፍላጎት የተነሳ እንጂ በአሜሪካና በንግድ ሸሪኮቿ ምጣኔ ሀብት መጎልበት የመጣ አለመሆኑን አመላክቷል፡፡

በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት ዓለማቀፋዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት እንደሚያከትምም እየተገለጸ ነው፡፡ አሜሪካ ተጽእኖ የምትፈጥርባቸው ዓለማቀፍ ተቋማትንና ስምምነቶችን አለማክበርና ራስን ማግለል እንደሚያዳክማትም ነው የተገለጸው፡፡ ከ “ፓሪስ” የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማፈንገጥ፣ ከፓስፊክ ተሻጋሪ አጋርነት (ትራንስ-ፓስፊክ ፓርትነርሺፕ)፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና ከነባሩ የአትላንቲክ ጥምረት ራሷን ማግለሏ በአብነት ተጠቅሰዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻልና በቅርቡ የተከሰተው ማኅበራዊ ቀውስ ከ1960ዎቹ (እ.አ.አ) ወዲህ ሀገሪቱ ዓይታ የማታውቃቸው ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ቀውሶች ደግሞ ከዓለማቀፋዊ መሪነቷ ለመውረዱ ማሳያ ሆነዋል፡፡

ምንም እንኳ ምጣኔ ሀብቷ ከመጪው ጥር አካባቢ ጀምሮ ሊያንሰራራ እንደሚችል ቢጠበቅም የቁጠባ አቅሟ በቀላሉ ይጠገናል ተብሎ አልተገመተም፡፡ የዶላር የመግዛት አቅም ከውጭ ንግድ አንጻር በመጪው ሐምሌ እስከ 35 በመቶ እንደሚወርድ መገመቱ ደግሞ ግሽበቱን ለመመከት ፈተና እንደሚሆንባት አስግቷል፡፡

Image may contain: 2 people

የአሜሪካ ዶላር የመግዛት አቅም እንደተተነበየው ከወረደ ደግሞ ሦስት አንኳር ጉዳዮችን ያስከትላል፤ ግሽበት፣ ለተወሰነ ጊዜ በግሽበት ውስጥ መቆየት እና ከቀውሱ ለማገገም ጊዜ መውሰድ፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ደግሞ የፋይናንስ ገበያውን በአዙሪት ውስጥ ሊያቆየው ይችላል፡፡ ይህም የአሜሪካን የንግድ ጉድለት ያሰፋዋል፡፡ የንግድ ድጎማ ሥርዓቷ፣ በተለይም ከቻይና ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ባላቸው 102 ሀገራት ላይ የምትከተለው አሠራር መልሶ ራሷን እንዳያዳክማትም ተሰግቷል፡፡

የዋሽንግተን ጊዜንና ሁኔታን ያላጤነ ከቻይና የሚጋፈፍ የፋይናንስ ጉድለት አሞላልም መጨረሻው የማገገሚያ ጊዜዋን ሊያራዝመው እንደሚችል ዘገባው ያስረዳል፡፡

ብሉምበርግ ዘገባውን ሲቋጭም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝንና የዘረኝነት ቀውሱ የዓለም ምጣኔ ሀብት አድራጊ ፈጣሪውን የአሜሪካ ዶላር መሪነት ያሳጣዋል፤ የአሜሪካንም ምጣኔ ሀብት የከፋ ቀውስ ውስጥ ያስገባዋል ብሏል፡፡

ዘገባው የአሜሪካ ዶላር ጥገኛ በሆኑ ሌሎች ሀገራት ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችልና ቀጣዩ የአሜሪካ ዶላርን የሚተካ መገበያያ ምን እንደሆነ አላመለከተም፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየሦስትዮሽ ድርድሩ ትናንትም ቀጥሎ መካሄዱን ሚኒስቴሩ አስታወቀ።
Next articleዋድላ በአለትም ይቀኛል፡፡