የጣና ፎረም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

7

ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጥቅምት 14 /2018 ዓ.ም የሚካሄደውን 11ኛው የጣና ፎረም የመሪዎች ስብሰባን አስመልክቶ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በባሕር ዳር ተወያይቷል።

የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾኖ በክልሉ የተካሄዱ ታላላቅ ሁነቶችን በሰላም ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል። አሁን ላይ የጣና ፎረም በሀገሪቱ እንዳይካሄድ የውጭ እና የውስጥ ኃይሎች ቢሠሩም እንኳን በተከናወነ ጥረት በክልሉ እንዲካሄድ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ፎረሙ በስኬት እንዲጠናቀቅም የጸጥታ መዋቅሩ በተቀናጀ መንገድ አካባቢውን ሊጠብቅ ይገባል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡም የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) የአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር በክልሉ የሚከናወኑ ታላላቅ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የሚያስችል ልምድ ማካበቱን ገልጸዋል።

በቀጣይ በክልሉ የሚከናወነው የጣና ፎረም በሰላም እንዲፈጸምም ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል እንዲያሳይ፣ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመኾን ደግሞ አካባቢውን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ
የኮሙዩኒኬሽን እና ሕዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም የሚካሄደው 11ኛው የጣና ፎረም በሰላም እንዲካሄድ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

ፎረሙ እስኪጠናቀቅ ድረስ በከተማው ውስጥ በተከለከሉ ቦታዎች ላይ ማንኛውም ሰው የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማችልም ገልጸዋል። ይዞ ከተገኘ በሕግ አግባብ ርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ የተለየ ነገር ከተመለከተ ለጸጥታ ወዋቅሩ እንዲያመለክት አሳስበዋል። የጣና ፎረም በባሕር ዳር መከበሩ ለክልሉ ትልቅ ዕድል በመኾኑ ማኅበረሰቡ ስብሰባው በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የጣና ፎረም የመሪዎች ስብሰባ እ.አ.አ በ2009 የወጣውን የትሪፖሊ ስምምነት ተከትሎ የተቋቋመ መድረክ ነው። የፎረሙ ዋና አላማ ደግሞ በአፍሪካ ላይ የሚስተዋሉ የጸጥታ፣ የሰላም እና የደኅንነት ሁኔታዎች ላይ በመወያየት ለአፍሪካ መፍትሔ ማፈላለግ ነው።

መድረኩ እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል። አስካሁን ከተካሄዱ አስር ፎረሞች ውስጥ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሄደው የ9ኛው ፎረም በስተቀር ሁሉም በባሕር ዳር ከተማ የተካሄዱ ናቸው።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጣና ፎረም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
Next article“ሰውነትን ያስቀደሙ፤ ለሀገር ሰላም የደከሙ”