
ሰቆጣ: ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ሌሎች እንግዶች ሰቆጣ ዙርያ ወረዳ በክላስተር የለማውን የመና ጤፍ አዝመራ ተመልክተዋል።
አርሶ አደር እባቡ ጌታሁን በሰቆጣ ዙርያ ወረዳ የ04 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል ያገኙትን የመና ጤፍ ዘርን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ማልማት እንደቻሉ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በባሕላዊ የአስተራረስ ዘዴ በመጠቀም የተለመደውን የጤፍ ዘር ያለሙ እንደነበረ አርሶ አደር እባቡ ትውስታቸውን አጫውተውናል። ሰፊ ማሳ ዘርተው ውስን ምርት ያገኙ እንደነበረ የገለጹት አርሶ አደሩ ከሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል ያገኙት የመና ጤፍ ዘር ግን በአጭር ጊዜ እና በውስን ዝናብ የሚደርስ ተስማሚ ዘር ነው ብለዋል።
“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” የሚሉት አርሶ አደሩ ባለሙት የ3 ሄክታር ማሳቸው እስከ 50 ኩንታል እንደሚጠብቁ ነው የጠቆሙት።
የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አዳነ ባሕሩ (ዶ.ር) በዋግ እና አካባቢው ተስማሚ ዘሮችን በምርምር በማስደገፍ ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በደጋማ አካባቢዎች የመና ጤፍ፣ የቁንጮ ጤፍ እና የመልካም ማሽላ ዘሮችን እንዲሁም በቆላማ አካባቢዎች ማሾ እና እንቁ ዳጉሳን በቴክኖሎጂ አስደግፈው እያላመዱ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት። በቀጣይም የዋግ ኽምራን አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የምርምር ማዕከሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
የዋግ ኽምራን ሥነ ምህዳር መሠረት ያደረገ ምርት ለማምረት የሰቆጣ ዝናብ አጠር የምርምር ማዕከል ከግብርና ተቋማት ጋር በመተባበር የሚሠራው ተግባር አበረታች መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብር መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሞገስ ኃይሌ ናቸው።
የመና ጤፍ በሄክታር እስከ 18 ኩንታል ምርት ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ምክትል ኀላፊው በአርሶ አደሮች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን በመስክ ጉብኝት ማረጋገጣቸውን ነግረውናል።
በመስክ ጉብኝቱ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ መሪዎች፣ የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተሮች እና ተመራማሪዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን