
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አባት የሠራውን ልጅ ያከብረዋል፤ አባት ያስረከበውን ልጅ ይጠብቀዋል። በዚያ ሥፍራ የታሪክ ብራና የመዘገባቸው፤ የታሪክ ቀለም ያረቀቃቸው፤ የታሪክ ተራራ የቆመላቸው ተቆጥረው የማያልቁ የኢትዮጵያ ታሪኮች በርካታ ናቸው።
እነዚያን ታሪኮች ማጥፋት አይቻልም። ጠፉ ሲባሉ በአመድ እንደተዳፈነ ረመጥ ተያይዘው ይነሳሉ። ተረሱ ሲባል በሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ልብ ይታወሳሉ። ተትተዋል አይነሱም ሲባል ሚሊዮኖች ተነስተው እንዴት የአባት እና የእናት ታሪክ ይተዋል ብለው ይመጣሉ።
በዚያ ሥፍራ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለሀገር ክብር ለሠንደቅ ፍቅር ሲሉ ወድቀዋል፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲሉ አያሌ የፈተና ዘመናትን አሳልፈዋል፤ በባሕር እና በየብሱ ለኢትዮጵያ ነጻነት በጽናት ቆመዋል። ሀገርን ሕያው አድርጎ ለማኖር እነርሱ በክብር አልፈዋል። ስሙ ከስማቸው፣ ታሪኩ ከታሪካቸው፣ ዘመኑ ከዘመናቸው ጋር የተሳሳረ ነው ቀይ ባሕር። ለዚያም ነው የሀገሬው ሰው እንዲህ የሚለው:-
” ድንጋይ ቢሳሳ መሮ አይበሳውም
የአባቱን ታሪክ ልጁ አይረሳውም” ይህ ታሪክ የአባት እና የእናት ታሪክ ነውና አይረሳም። አይዘነጋም። ፈጽሞ ሊዘነጋም አይችልም።
በቀይ ባሕር የበዙ የኢትዮጵያ መርከቦች ሲመላለሱ ኖረዋል። ከአንደኛው የምድር ጫፍ ወደ ሌላኛው የምድር ጫፍ ተጉዘዋል። የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ልክ፣ የሃብት መጠን፣ የክብር እና የታላቅነት ደረጃን ለዓለሙ ሁሉ ሲነግሩ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ታሪክ ሲገለጥ እንደ ጀንበር የሚያበሩ ሥልጣኔዎች ይገለጣሉ። ሥልጣኔዎቹ ደግሞ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዙ ናቸው።
የኢትዮጵያን ታሪክ ከቀይ ባሕር፣ የቀይ ባሕርንም ታሪክ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር መነጣጠል አይቻልም። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ባሏት የበዙ ወደቦቿ ንግዷን ስታጧጡፍ ኖራለች። በቀይ ባሕር ላይ የገነኑ የንግድ መርከቦች፣ የተፈሩ የጦር መርከቦች፤ የንጉሡ እና የንግሥቷ የክብር መቀመጫ ጀልባዎች እና መርከቦች የነበሯት ገናና ሀገር ናት። ቀይ ባሕርን በዓለም አቀፍ ጫናዎች፣ በቀጣናው የፖለቲካ ሸፍጦች፣ በውስጣዊ የፖለቲካ ስህተቶች ከማጣቷ አስቀድሞ የኢትዮጵያ የንግድ እና የጦር መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ መልሕቃቸውን ጥለው ኖረዋል። የጦር መርከቦቹ ሰላሟን፤ የንግድ መርከቦቹ ደግሞ የንግድ ሥርዓቷን ሲያስጠብቁ ዘመናትን ተሻግረዋል።
ቀይ ባሕርን ካጣች በኋላ ግን እልፍ ነገር አጥታለች። አሁን ላይ ኢትዮጵያ የራሷ የኾነውን ነገር ግን በታሪክ አጋጣሚ አጥታው የቆዬውን የቀይ ባሕር ይመለስ ዘንድ ግልጽ ጥያቄ ጠይቃለች። አሁን ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከባሕራቸው ቀይ ባሕር ላይ ዓይናቸውን ጥለዋል።
በቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል። የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል የተቀላቀሉት በንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነበር። ከዚያ ዘመን ጀምረው ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ይዞታዋን እስክታጣ ድረስ በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ ኾነው ሀገራቸውን አገልግለዋል። የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሲፈርስም እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ወታደር ሲቆጩ ኖረዋል።
ኮሞዶር ጥላሁን መኮንን ይባላሉ። ማዕረጋቸው ከምድር ጦር ጋር ሲነጻጸር ብርጋዴር ጄኔራል ማለት ነው። የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል የተቀላቀልኩት በ1954 ዓ.ም ነበር፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ድረስ ቆይቻለሁ ይላሉ። በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ በመሪነት ረዘም ላለ ጊዜ አገልግለዋል። መርከቦችን አዝዘዋል፤ በቀይ ባሕር ላይ ሀገራቸው የሰጠቻቸውን አደራ ለመወጣት በትጋት አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ የጦር መርከቦች ላይ ኾነው በቀይ ባሕር የተለያዩ ግዳጆችን ፈጽመዋል። በተለይም ኢትዮጵያ ከተሰኘችው የጦር መርከብ ጋር ትዝታ አላቸው።
ኢትዮጵያ የተሰኘችው የጦር መርከብ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በኋላም ርእሰ ብሔሩ በሚመጡ ጊዜ የሚቀመጡባት ነበረች። የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የኢትዮጵያን የባሕር ክልል የሚጠብቅ ነው። ምጽዋ እና አሰብ ላይ መደቡን ያደረገው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በቀይ ባሕር በኩል ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት ለመመከት በተጠንቀቅ የቆመ ነበር።
ምጸዋ ላይ መደቡን ያደረገው የሰሜን ባሕር ኃይል ዕዝ፣ የአሰቡ ደግሞ የደቡቡ ባሕር ኃይል ዕዝ እየተባለ ይጠራ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዋናው የባሕር ኃይል ማዘዣ ደግሞ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ዋና ማዘዣ አስመራ ላይ ኾኖ እንደነበርም አስታውሰዋል። ነገር ግን ምቹ ስላልነበር ዋና ማዘዣ ጣብያው ወደ ዋና ከተማዋ ተመለሰ ይላሉ።
የባሕር ኃይል ማሠልጠኛ ማዕከሎች እና ኮሎጆችም ነበሩ ይላሉ። እርሳቸውም በምጽዋ የባሕር ኃይል ኮሌጅ እንደሠለጠኑ ያስታውሳሉ። የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል በየጊዜው ራሱን እያደረጀ የሄደ፣ በቀይ ባሕር ቀጣና ታላቅ አቅም የነበረው ነው ይላሉ። ምን አልባትም በአፍሪካ ጠንካራ ከሚባሉ የባሕል ኃይሎች መካከል አንደኛውም ነበር።
በባሕር ኃይል የትም ውቅያኖስ ሄዶ መንቀሳቀስ የሚችል ባሕር ኃይል ያለው ሰማያዊ ባሕር ኃይል (blue Navy) ይባላል። አካባቢውን ወይም የባሕር ክልሉን ብቻ የሚጠብቅ ከኾነ ደግሞ ቡናማ ባሕር ኃይል ( Brown Navy) ይባላል። የኢትዮጵያ የባሕር ኃይልም በየትኛውም ውቅያኖስ የመንቀሳቀስ አቅም ያለው ስለነበር ሰማያዊ ባሕር ኃይል ( blue Navy) ነበር። በዚህም ደረጃው ነው እስከመጨረሻው የቆዬው ይላሉ።
ኢትዮጵያ በባሕር ኃይል የታጠቀች ነበረች። ታዲያ ያን የመሰለ ባሕር ኃይል ሲፈርስ ሀዘኑ እና ቁጭቱ ከባድ ነበር ነው የሚሉት። እኛ ያጣናነው አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የባሕር ክልል ነው፤ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የኢትዮጵያን የባሕር ክልል ተቆጣጥሮ ሀገሩን ሲጠብቅ የኖረ ነው። ያን የመሰለ የባሕር ክልል ማጣት፣ ያን የመሰለ የባሕር ኃይልም ማፍረስ በጣም ያስቆጫል ነው የሚሉት።
ኢትዮጵያ በታሪክ እንደርሷ ሁሉ ቀደምት ሥልጣኔ ከነበራቸው ከሮማውያን፣ ከፐርሺያ እና ከሌሎች ጋር የምትገናኝበት፣ የምትወዳደርበት፣ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ ያለው የባሕር ክልል የምትቆጣጠርበት የባሕር ኃይል የነበራት ገናና ሀገር ነበረች።
በባሕር ኃይል ላይ የነበራትን ኃያልነት የሚፈታተኑ ፈተናዎች በየዘመናቱ ነበሩባት። የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች ገናና እና ተፈሪ የነበሩት በባሕር አማካኝነት ባለው ሀብቷ ነበርና የባሕር ክልሏን ለማስጠበቅ ለዘመናት ስትታገል ኖራለች። በልጆቿም ስትጠበቅ ዘመናትን ተሻግራለች።
አሁን ኢትዮጵያ ያጣችው የባሕር በር ብቻ አይደለም፤ የባሕር ክልሏን ጭምር እንጂ። ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንድታጣ የውጭ ጠላቶች፣ ተገንጣዮች፣ የሀገር ውስጥ ብሔርተኞች ተረባርበዋል። ጠላቶች ከውስጥ እና ከውጭ፣ ከግራ እና ከቀኝ፣ ከፊት እና ከኋላ ኾነው ኢትዮጵያን ባሕር አልባ አደረጓት።
እኒያ የባሕር ኃይል ምድቦች፣ በየትኛውም ውቅያኖስ የሚመላለሱ የኢትዮጵያ መርከቦች እንደዋዛ የሚያልፉበት ዘመን መጣ። ይህ እንኳን በባሕር ኃይል ውስጥ ለዓመታት ለቆየ ወታደር ይቅርና በአሻገር ኾኖ የኢትዮጵያን ዝና ለሚሰማ አንድ ኢትዮጵያዊ እንኳን እንደ እግር እሳት ይፋጃል።
የባሕር ክልልን የማጣት አደጋ በተደቀነ ጊዜ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል እና ሌሎች የኢትዮጵያ ጀግና ወታደሮች የኢትዮጵያን ባሕር በር ለማስጠበቅ አያሌ መስዋዕትነት ከፈሉ። ኢትዮጵያ ባሕር በር አጥታ ስትኖር ከማየት ባሕር ይብላን እያሉ ራሳቸውን በቀይ ባሕር ላይ አጠፉ። ነገር ግን ጠላት በዝቶ፤ ጊዜው ለጠላቶች አዘንብሎ ነበርና ባሕር በሩን ማስቀረት ሳይችሉ ቀሩ። እኒያ ታላላቅ መርከቦችም ታሪክ ኾኑ።
ዓመታት እንደዋዛ ነጎዱ። ኢትዮጵያም ከጥንተ ሃብቷ ተለይታ ባይታዋር ኾና ኖረች። የራሷ በነበረ ባሕር ላይ እንግዳ ኾና አገልግሎት ለማግኘት አያሌ ገንዘቦችን ፈሰስ አደረገች። ይህም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን የእግር እሳት ኾኖ ኖረ።
ሌላ ዘመን መጣ። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን እንደ እግር እሳት ሲፈጃቸው የኖረውን ሃሳብ በአደባባይ አወጡት። የተዳፈነውን እሳት አያያዙት። አሁን የቀደመውን ባሕር ኃይል ክብርና ዝና የሚመልስ የባሕር ኃይል እንደገና ተቋቁሟል። ይህ ባሕር ኃይል ሲቋቋምም ኮሞዶር ጥላሁን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ነግረውናል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት አለባት የሚለው ጥያቄ ትክክል ነው፤ ይሄን ያክል ሕዝብ ይዞ ያለ ባሕር በር መኖር አይቻልም፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት አለባት፤ ባሕር ኃይልን የመሠለ ታላቅ ተቋም ማፍረስ፤ የባሕር ክልልንም አሳፎ መስጠት የሚያስቆጭ ነበር፤ አሁን ባሕርን መልሶ ለማግኘት እየተደረገ ያለው ጥረት አስደስቶኛል ነው የሚሉት።
ባሕርን መልሶ ለማግኘት የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፤ ለቀጣናው አዋጭ የሚኾነው የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በአወንታ መመልከት፤ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ዕድል መስጠት ይገባል፤ ኤርትራ ኢትዮጵያን በወዳጅነት እንጂ በጠላት ማየት የለባትም፤ ጥያቄውን መረዳት እና የኢትዮጵያን እውነት መገንዘብ ይገባታል ነው ያሉት።
አሁን ዓይኖች ሁሉ ቀይ ባሕር ላይ አነጣጥረዋል፤ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ታሪክ የተጻፈበት፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የተረቀቀበት፣ የኢትዮጵያ ከፍታ በዓለሙ ሁሉ የገነነበት ነውና። ቀይ ባሕርን ከኢትዮጵያ ታሪክ መነጠል አይቻልም፤ ከእርሷም አርቆ ማኖር አይታሰብም።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!