የሦስትዮሽ ድርድሩ ትናንትም ቀጥሎ መካሄዱን ሚኒስቴሩ አስታወቀ።

200
Ethiopia's Grand Renaissance Dam is seen as it undergoes construction work on the river Nile in Guba Woreda, Benishangul Gumuz Region, Ethiopia September 26, 2019. Picture taken September 26, 2019. REUTERS/Tiksa Negeri - RC1BF04BBB80

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ እንደገና የተጀመረው ድርድር ትናንትም ቀጥሎ ውሏል።

የትናንት ውሎውን ድርድር አስመልክቶ የኢፌዴሪ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንደገለጸው ኢትዮጵያ በድርድሩ ሁለት የቴክኒክና የህግ ቡድኖች ቢኖሩ በሚል ያቀረበችውን ሀሳብ ሱዳን ተቀብላለች።

ግብፅ ደግሞ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሳትቀበለው የቀረችውን ረዘም ያለ የድርቅ ጊዜን እና ደረቃማ ዓመትን በተመለከተ ዝርዝር ህግ መኖር አለበት የሚለውን ሃሳቧን በድጋሚ ማቅረቧን አስታውቋል።

በእለቱ በነበሩ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተካሄደ ድርድር ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ባቀረበችው ሃስብ ላይ ንግግር መደረጉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ዙር የግድቡን የውሃ አሞላል እና አሞላሉ የሚገዛበት መመሪያን በተመለከተ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሃሳብ ለመቀጠል ከመግባባት መደረሱን አስታውቋል።

ረዥም ድርቅን በተመለከተ የቴክኒክ ኮሚቴ የውኃ አለቃቁ ላይ ህግ እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት እንዲሰጠው እና ዝርዝር አለቃቀቅን በተመለከተ ግን ድርድር እንደሚያስፈልግ ከመግባባት ላይ ተደርሷል ብሏል ሚኒስቴሩ። የግድቡን ደህንነት የተመለከተም ህግ እና ግድቡ በሚኖረው አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ተፅእኖ ጥናት ማስፈለግ ላይ መግባባታቸውንም መግለጫው አመላክቷል።

Image may contain: one or more people, mountain, sky, outdoor and nature

የግብፅ ተደራዳሪዎች በእለቱ የነበራቸው ተሳትፎ የተቀዛቀዘ ነበር ያለው መግለጫው ከተራዘመ የድርቅ ሁኔታ ጋር ያላቸውን ፍላጎት በማሳወቁ ላይ ብቻ መሳተፋቸውን አመልክቷል።

ሆኖም በመጨረሻ ሰዓት የግብፅ ተደራዳሪዎች ውይይት ሲደረግበት በነበረው እና ከዚህ በፊት ራሳቸው ሊያሰራ የሚችል ሰነድ ነው ብለው አስተያየት የሰጡበትን ሱዳን ያቀረበችውን ሰነድ መልሰው ተቃውመዋል ብሏል ሚኒስቴሩ።

በተጨማሪም የራሳቸውን አቋም ይዘው እንዲቀርቡ መጠየቃቸውን የተቃወሙት ግብፃውያኑ ድርድሩ እየተካሄደ የግድቡ ውኃ ሙሌት ሊካሄድ አይገባም ሲሉም ተቃውመዋል። እየተካደ ያለው ድርድር ሰኞ እንዲጠናቀቅ እና እስካሁን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያስቀመጧቸውን በድርድሩ የተገኙ ለውጦች እውቅና ላለመስጠት ፍላጎት ታይቶባቸዋል ብሏል መግለጫው።

ድርድሩ ቀጥሎ ሲካሄድም የእስካሁን ድርድሮችን መሠረት በማድረግ በተዘጋጁ መመሪያዎች እና ህጎች ላይ ሀሳብ እንደሚለዋወጡ የሚኒስቴሩን መግለጫ ዋቢ አድርጎ ፋብኮ ዘግቧል።

ነገም በእስካሁኑ ድርድር የተገኙ ለውጦችን በመገምገም ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ድርድሩ እንደሚቀጥል ታውቋል።

Previous articleየቻግኒ የዳልጋ ከብት ብዜትና ዝርያ ማሻሻያ በገንዘብ ችግር ምክንያት ተገቢውን ጥቅም መስጠት እንዳልቻለ ማዕከሉ አስታወቀ፡፡
Next articleየአሜሪካ ዶላር ቅቡልነት ማክተሚያ እየተቃረበ መሆኑን ብሎምበርግ ዘገበ፡፡