
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራችን እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች ምክንያት አንዱ ምናልባትም ዋነኛው የአገልግሎት አሰጣጥ ድክመት መኾኑን አስባለሁ፡፡
የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በየጊዜው መዳከም እንጂ እንደሚፈለገው ስር ነቀል መሻሻሎች አይታይበትም፡፡ ስልት የሚቀያይሩ ብልሹ አሠራሮች መፈብረካቸው ፀሐይ የሞቀው ነው፡፡ በሰዓቱ በቢሮ አለመገኘት፣ ፈጣን ግልጋሎት አለመስጠት፣ አላግባብ ክፍያ መጠየቅ፣ አድልዎ፣ ተገልጋይን አለማክበር እና ሌሎችም የሥነ ምግባር ብልሽቶች ኅብረተሰቡን ያማረሩ እና ተስፋ ያስቆረጡ ኾነዋል፡፡
የችግሮቻችን አንዱ ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጥ መዳከም መኾኑን በስብሰባዎች እና በመገናኛ ብዙኀን ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡ መነገር ብቻም ሳይኾን ስምምነት ላይ ተደርሶበታል፡፡ መፍትሔውም ሕዝብን በቅንነት እና በትጋት ማገልገል እንደኾነም ታምኖበታል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ችግሮችን በመቅረፍ ኅብረተሰቡ ተገቢውን ግልጋሎት እንዲያገኝ፣ መልካም አሥተዳደር እና ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲፋጠን በትኩረት እየሠራ መኾኑን እየገለጸ ነው፡፡
ትዝብቴን በሁለት የባሕር ዳር ክፍለ ከተሞች የገቢዎች፣ በአንድ የፖሊስ እና በአንድ የፍትሕ አገልግሎት አድርጌያለሁ።
በመጀመሪያው ቀን ትዝብቴ በዕለቱ በከተማ አሥተዳደሩ የተጠራ ስብሰባ ምክንያት ከገቢዎች ጽሕፈት ቤት በስተቀር ሁለም ተቋማት ዝግ ናቸው፡፡ የገቢዎች ጽሕፈት ቤቱ በተገልጋዮች ተጨናንቋል፡፡
የገቢዎች አገልግሎት እንዳይቋረጥ መደረጉ የሚበረታታ ቢኾንም ሌሎች ተቋማት ግን መረጃ ሰጪ እንኳ ሳይቀር ዝግ መኾናቸው አገልግሎት የሚሰጠው ለገንዘብ ስብሰባ ብቻ ነው እንዴ አስብሎኛል፡፡
ተገልጋዩ በመስኮት እና በበር አካባቢ ቆሟል፤ ወረፋ የሚያሲዝ የለም፤ እያንዳንዱ በሚያውቀው እና ያዋጣኛል በሚለው አማራጭ ለመገልገል ይሞክራል።
እኔም አንዷን ሠራተኛ ጠጋ ብየ ለግብር መክፈል ፋይል ልከፍት እንደፈለግኩ ነገርኳት፤ ነገ ና አለችኝ።
በሌላ ቀን በሌላ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ምልከታዬም ተገልጋይ እየተጉላላ ”አሁን ወጣ አለ” የሚባሉ ሠራተኞችን ታዝቤያለሁ።
የሥራ ክፍሎችን የሚገልጽ የበር ላይ ጽሁፍ ቢኖርም ተገልጋይ በመስኮት ተደራርቦ ያለ ወረፋ ለመስተናገድ ይራኮታል። አንዳንዱም ውስጥ ዘልቆ ፋይሉን ራሱ ሲፈልግ አይቻለሁ።
ሠራተኞች ፋይል ይዘው ሌላ ክፍል ይሄዱና ቆይተው ይመለሳሉ። አንዱ ሠራተኛ ሌላ ክፍል ”ለሥራ” ቆይቶ ሲመለስ ከተገልጋይ ጋር ተዘላለፈ። ቆይቼ ያንን ተገልጋይ ”ምን ኾናችሁ ነው የተጣላችሁት?” አልኩት።
በቅሬታ ስሜት ”እንተዋወቃለን!” ብቻ ብሎኝ ዝም አለ። ተበሳጭቶ ነው።
ግብር ከፋዮች ለፋይል መክፈት፣ ግብር ለመክፈል ወይም ለይግባኝ ይጣደፋሉ። አብዛኞቹ ደስተኛ አይደሉም። የሚያስተናግደኝ አጣሁ፤ አልተባበረኝ አሉ፤ ወዘተ በማለት ያማርራሉ።
ከደንበኛው እና ተገልጋዩ ብዛት የተነሳ ፋይሎች ተከምረዋል። ከዚያ ፋይል እየፈለጉ መሥራት ጊዜ ያባክናል፤ ሠራተኛንም ያደክማል።
ድክም ያላቸው፣ የተሰላቹ፣ እንኳን ምን ልታዘዝ ሊሉ ተጠይቀውም ፈጥነው ምላሽ የማይሰጡ ሠራተኞች በሁለቱም ክፍለ ከተሞች የገቢዎች ትዝብቴ አስተውያለሁ።
ምንም እንኳ ከተገልጋዮችም ያልተገቡ ፍላጎቶች እና ቅሬታዎች ቢኖሩም ሠራተኞች የሥራውን እና የተገልጋዩን ባሕሪ ተረድተው፤ አገልጋይነታቸውንም ሳይረሱ ትህትና ሊኖራቸው ይገባል።
አንዱን ጠጋ ብየ ምንኾነህ ነው አልኩት። የተለያዩ የቁም ሥራዎች እንዳሉት፣ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ ግብር መክፈል ቢፈልግም የሚያስተናግደው ባለሙያ የለም መባሉን ነገረኝ። ይብሰከሰካል።
”እና ምን ተሻለ?” አልኩት፤
”ኧረ ተወኝማ!” ነበር መልሱ።
ወሬውን ሳይጨርስልኝ ”ሄሎ! ሄሎ!…” በማለት ተቻኩሎ ከግቢው ወጥቶ ሄደ።
የተገልጋዮች መቀመጫ በቂም፣ ምቹም አይደለም፡፡ ግብር ከፋዮች በበር እና መስኮት ይጋፋሉ፡፡ በመጀመሪያው የገቢዎች ጽሕፈት ቤት አቅጣጫ ጠቋሚ ጽሑፍም የሚያስተባብር የለም፤ በሁለተኛው ቢያንስ የሥራ ክፍሉን ማንነት ጠቋሚ ጽሑፍ በየበሩ አለ።
ግብር ከፋይ ፈጣን እና ምቹ አገልግሎት ባጣ ቁጥር ወዳልተገባ መስመር እንደሚሄድም የሚያሰጋ ነገር ታዝቤያለሁ።
በፍትሕ ተቋሙ ስገለገል ደግሞ አራት ሠራተኞችን ያገኘሁ ሲኾን ሁሉም ”የአንድ መስኮት አገልግሎት” በሚባለው ውስጥ ይገኛሉ። ይህም ለተገልጋይ የሚመች ነው።
የሕግ አገልግሎት ሲሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ቢኾንም ተገልጋይን በአካላዊ ዕይታ ገምቶ መፈረጅ እና ያለምክንያት በመጠራጠር አላስፈላጊ መረጃ ሲጠይቁም ተመልክቻለሁ፡፡ ይህም ለተገልጋይ ክብር አለመስጠት ነው።
ለመንግሥት ሥራ በፖሊስ ተቋሙ ሄጄ እንዳየሁት ደግሞ በአጥር እና የቢሮ በር ጥበቃዎች “ማንን ፈልገህ ነው” የሚል ጥያቄ እና የደኅንነት ፍተሻ እንጂ እንቅፋት አልገጠመኝም። “ሁሉም እንደዚህ ይኾኑ?” ስል በውስጤ ጠየቅኹ።
ከሚዲያ ስለሄድኩ ወይም በተፈጥሯቸው ቅን አገልጋይ ኾነው ፈጣሪ ይወቀው በአጭሩ ከኀላፊው ተወያይተን ተስተናገድሁ።
በየተቋማቱ የጥበቃ ሠራተኞች እና ሌሎች ጥቂት ባለሙያዎች ተገልጋይን ቀርበው በማነጋገር የቸግሩ መፍትሔ ለመኾን ሲሞክሩም አይቻለሁ። በዚህም አገልጋይ ጨርሶ አለመጥፋቱን ታዝቤያለሁ።
አገልግሎት ፍለጋ እና ለምልከታ በሄድሁባቸው የገቢዎች እና ሌሎች ተቋማት በአመዛኙ ያየሁት በስብሰባ እና በብዙኀን መገናኛ ድርጅቶች ቃል እንደሚገባው አይደለም፡፡ የሥራ ኀላፊዎች “ለክትትል እንመጣለን፤ ጠብቁን” ከማለት ይልቅ በድንገት እና በስውር ቢፈትሹ መልካም ነው፡፡ ቀንድ ያወጣውን ችግር ለማስተካከል ያስችላቸዋልና።
በዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!