
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዛሬው ሳምንቱ በታሪክ ክቡር ዶክተር ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁን እናስታውስ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሥነ ጽሑፍ፣ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ታላቅ ሰው ናቸው።
ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ጥቅምት 05/1902 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር፣ በደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ በጎዛመን ወረዳ ነው የተወለዱት።
ገና በልጅነታቸው በቤተ ክርስቲያን ትምህርት በተለይም በጎጃም ገዳማት (ደብረ ኤልያስ፣ ደብረ ወርቅ፣ ዲማ) የቅኔ ትምህርትን አጠናቅቀዋል። በኋላም አዲስ አበባ መጥተው በስዊድን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት እና በራስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተምረዋል።
ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ከአርበኞች ጋር ተቀላቅለው ሲዋጉ ቆይተዋል። ተማርከውም በጣሊያን የፖንዞ እና ሊፓሪ ደሴቶች ለሰባት ዓመታት ያህል በግዞት ቆይተዋል። ከግዞት ከተመለሱ በኋላ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ቀጥለዋል።
ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በመንግሥት አሥተዳደር ውስጥም በዳይሬክተርነት፣ በምክትል ሚኒስትርነት፣ በትምህርት ሚኒስትርነት፣ በዕቅድ እና ልማት ሚኒስትርነት፣ እንዲሁም በሴናተርነት የመንግሥት ከፍተኛ ኀላፊነቶች ላይ አገልግለዋል።
ዲፕሎማቱ ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በኢየሩሳሌም ቆንስል፣ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሁም በታላቋ ብሪታንያ እና በኔዘርላንድስ አምባሳደር በመኾን ሀገራቸውን ወክለዋል።
ከፍ ብለው በተቀመጡበት የሥነ ጽሑፍ ዘርፍም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰው ናቸው ከሚታወቁባቸው ሥራዎቻቸው መካከልም ፍቅር እስከ መቃብር (1958 ዓ.ም)፣ ወንጀለኛው ዳኛ (1970 ዓ.ም)፣ የልም ዣት (1980 ዓ.ም)፣ “ያበሻ እና የወደኋላ ጋብቻ” የተሰኘ የተውኔት ድርሰት እንዲሁም “ትዝታ” እና “ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አሥተዳደር ያስፈልጋታል?” የተሰኙ ሥራዎችን አበርክተዋል።
ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ለሀገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተርነት ማዕረግ ሰጥቷቸውም ነበር። እኒህ ታላቅ ሰው ኅዳር 26/1996 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ነው ያረፉት።
የመረጃ ምንጭ ፦ ዘብላክ ላየን መጽሐፍ

ሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የሥነ ጥበብ ሰው ቀዳሚው ሰው ናቸው። የዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ አባት በመባልም በዘርፉ በጉልህ የሚነሱ ሰው ናቸው። እኒህ ታላቅ የሥነ ጥበብ ሰው ውልደታቸው በዚህ ሳምንት ነው።
ጥቅምት 05/1924 ዓ.ም በሐረር ከተማ የተወለዱት ሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በጀርመን ሀገር ሥዕልን አጥንተዋል። ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም አብስትራክት ኤክስፕሬሽኒዝም (Abstract Expressionism) የተባለውን ዘመናዊ የሥዕል ስልት በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን የሥነ ጥበብ ዓለም ለውጠዋል።
ሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በሥዕል ብቻ ሳይኾን በግጥምም ይታወቃሉ። ግጥሞቻቸው እንደ ሥዕሎቻቸው ሁሉ አዲስ እና ልዩ አተያይ ላይ የሚያተኩሩ በመኾናቸው ሰዎችን ብዙ አወያይተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መምህር በመኾን ለብዙ አርቲስቶች አስተማሪ እና አርዓያ መኾን የቻሉ ሰውም ናቸው ሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ።
የሥራዎቻቸው ማዕከል የኾነው የገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከልም በአዲስ አበባ ከተማ ይገኛል።
እኒህ የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ባለውለታ ሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኦክላሆማ እያሉ ማረፋቸውን ታሪካቸው ያስረዳል።
ሥዕሎቻቸው እና ግጥሞቻቸው ግን ብዙ አተያይ ያሳዩ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ጥበብ ትልቅ አሻራ ጥለው ያለፉ ድንቅ የጥበብ ሰውም ናቸው።
የመረጃ ምንጭ ፦ ዘብላክ ላየን መጽሐፍ

በዚህ ሳምንት በሚከበረው የገጠር ሴቶች ቀን የቤተሰብ ኀላፊነትን ተሸክመው ሀገርን ለማቅናት ደፋ ቀና የሚሉትን ሴቶች እናነሳቸዋለን።
የዓለም የገጠር ሴቶች ቀን (International Day of Rural Women) በየዓመቱ ጥቅምት 05 ነው የሚከበረው። ይህ በዓል እንዲከበር እና ለገጠር ሴቶች ምሥጋና እንዲቀርብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የወሰነው ታኅሣሥ 18/2007 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ በውሳኔ ቁጥር 62/136 እንዲከበር መወሰኑን ታሪኩ ይነግረናል።
ይህ በዓል ለእነዚህ ጠንካራ የገጠር ሴቶች ከሚቀርበው ምሥጋና ባሻገር በግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና በዘላቂ ልማት ውስጥ የገጠር ሴቶች የሚጫወቱትን ሚና ማጉላት ዋነኛው ዓላማው ነው።
ለቤተሰቦቻቸው፣ ለማኅበረሰባቸው እና ለዓለም ምግብን በማምረት፣ በማቀነባበር፣ በማዘጋጀት እና በማሠራጨት ወሳኝ ሥራዎችን በመሥራትም ከፍ ያለውን ድርሻም ይወስዳሉ።
ቀኑ ሲከበርም የገጠር ሴቶችን አቅም ማጎልበት ድህነትን፣ ረሃብን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ወሳኝ መኾኑን በጉልህ ለማሳሰብ በእጅጉ ይረዳል።
የመረጃ ምንጭ፦ ዩ ኤን ውመንስ ኦርግ
ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!