
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 08/2018(አሚኮ) የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች ማኅበር እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር “ለአማራ ክልል ሰላም መስፈን የሰላም እናቶች ሚና ” በሚል መሪ መልዕክት ምክክር አካሂደዋል።
የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለሰላም ያላቸው ሚና ትልቅ እንደኾነ ተናግረዋል። ሙሉ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ እናቶች በመድረኩ መገኘታቸውንም ጠቅሰዋል።
በሰላም መደፍረስ ውስጥ ያሳለፍነው ጊዜ የውድመትና የማነስ ነው ብለዋል። አሁን ላይ እናቶች ኢትዮጵያውያንን ወደ ከፍታ እና ወደነበርንበት የመመለስ፣ ወንድማማችነትን የመገንባት፣ ጉርብትናን የማክበር፣ ኢትዮጵያዊነትን የመገንባት ሀሳብ ይዛችሁ ስለመጣችሁ ይህንን ተከትለን እንሠራለን ነው ያሉት። አብረን ለሰላም እንሠራለን ብለዋል።
የሰላም እናቶችን ጨምሮ ለክልሉ ሰላም አስተዋጽኦ እያደረጉ ለሚገኙ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዴስክ ኀላፊ ወንደሰን መኮነን ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባሕል፣ በፖለቲካ እና በተለያዩ አመለካከቶች ሊለያዩ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ከዚህ በፊትም የውስጥ ችግሮች አጋጥሟቸው እንደሚያውቅ ተናግረዋል። ነገር ግን ጠላት ብሔራዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ ክብርን ለመድፈር ባሕር ተሻግሮ ሲመጣ በኢትዮጵያዊ አርበኝነትና አንድነት የውስጥ ችግሮቻቸውን በይደር አቆይተው ጠላትን መክተው አኩሪና የተከበረች ሀገርን አስረክበውናል ነው ያሉት።
አሁንም ኾነ ወደፊት የውስጥ ችግሮች ይኖራሉ ያሉት ኀላፊው ችግሮችን መቆጣጠሪያ መንገድ የሰላም አማራጮችን በመጠቀም ሊኾን እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ከሰላም ውጭ አማራጭ የለም፤ ከሰላም ውጭ ያሉ አማራጮች በሙሉ አውዳሚና አክሳሪ ናቸው፣ ለማንም አይጠቅሙም፤ ማንንም አሸናፊ አያደርጉም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ግጭቶች ሲፈጠሩ የሚፈቱበት ቱባ ባሕሎች እንዳሏቸውም አንስተዋል። የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች ማኅበር እየሠራ ያለውም ይኽንኑ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
የሰላም እናቶች ግጭት ይብቃ በማለት የሰላም ሚኒስትርን እያገዙ እና ሀገራቸውንም እያገለገሉ እንደኾነም ተናግረዋል። አሁን ላይም በችግሮች መካከል ሰላምን መፈለግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል። ለሰላም ሲባል ሁለንተናዊ አቅሞችን መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን