በአማራ ክልል የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ሞዴል ለማድረግ ይሠራል።

10

አዲስ አበባ: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘውን የኀይሌ ማናስ አካዳሚ አዳሪ ትምህርት ቤትን የመማር ማስተማር ሂደት ተመልክተዋል።

የኀይሌ ማናስ አካዳሚ አዳሪ ትምህርት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ክፍሌ አካዳሚው ከመላ ሀገሪቱ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎችን እየተቀበለ በማስተማር በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈተነው አካዳሚው ሁሉንም ተማሪዎች በከፍተኛ ውጤት ከማሳለፍ ባለፈ ዓለምአቀፍ ዩንቨርሲቲዎችን የተቀላቀሉ ተማሪዎችን አፍርቷል ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች መደበኛ ትምህርት ከማስተማር በተጨማሪ ተማሪዎችን በሕይወት ክህሎት፣ በሀገር ግንባታ እና ስነ ባሕሪ ላይ ኢትዮጵያዊነትን በተግባር እንዲያሳዩ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

ኀይሌ ማናስ አካዳሚ ከተቀበላቸው ተማሪዎች በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ወደ ግቢ በመጥራት የማጠናከሪያ ትምህርት እና የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን እየፈጠረ ያለው አካዳሚው ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት በዘለለ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ እንዲቀረጹ እና ሕይወታቸውን በራሳቸው እንዲመሩ የሚያደርግበት ስልት የሚደነቅ ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ያላቸው ሀገራዊ ስሜት እና ቀጣይ የሕይወት አቅጣጫቸውን እየቀረጹ ያሉበት መንገድ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ተስፋ የሚያለመልም መኾኑን ገልጸዋል።

ኀይሌ ማናስ አካዳሚ በክልሉ ካሉ የትምህርት ተቋማት ምሳሌ በመኾኑ ሌሎች በመንግሥት የሚሠሩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በዚህ ልክ እንዲኾኑ እንሠራለን ብለዋል።

ከአዳሪ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ ሌሎች 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማሻሻል አሁን ያሉ ችግሮችን በማስተካከል የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍና በቀጣይ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ኀይሌ ማናስ አካዳሚ በ2017 ዓም 12ኛ ክፍል ያስፈተናቸውን 36 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ አሳልፏል።

ከ36ቱ ተማሪዎች መካከል 29 ተማሪዎች ከ500 ነጥብ በላይ ያመጡ ናቸው። 30 ተማሪዎች ደግሞ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል ማግኘት መቻላቸው ተገልጿል።

ዘጋቢ:- አደራው ምንውዬለት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበኮምቦልቻ ከተማ 127 ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ ናቸው።
Next articleከሰላም ውጭ ያሉ አማራጮች በሙሉ አውዳሚና አክሳሪ ናቸው።