
ደሴ: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት የደብረብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጂ ዲን መባ ፈጠነ (ዶ.ር) ኮሌጁ የተሰጡትን ዋና ዋና ተግባራት መንግሥት በሚመድበው በጀት ብቻ ማከናወን ስለማይቻል የውስጥ ገቢን የሚያሳድጉ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።
የኮሌጁ መምህራንም ችግር ፈቺ ጥናት እና ምርምሮችን በማካሄድ ለችግሮች ሳይንሳዊ መፍተሔዎችን እንዲያመላክቱ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጂ ዲን ሀሰን ወርቁ (ዶ.ር) ኮሌጁ የቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ የሥነ ጥበብ ማዕከል እና የሳይንስ ቤተ ሙከራ ላይ በትኩረት መሥራቱን ገልጸዋል። ከተለያዩ ኮሌጆች ለመጡ የሥራ ኀላፊዎችም ልምዳቸውን ማጋራታቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት የሚመደቡላቸውን ሠልጣኞች ተቀብለው ብቁ መምህራን ኾነው እንዲወጡ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውንም የሥራ ኀላፊዎቹ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደምስ እንድሪስ ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት ምክንያት በእጅጉ ከተጎዱት ዘርፎች ውስጥ ትምህርት አንዱ መኾኑን አንስተዋል።
ይህንን ችግር ለመቀልበስ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማይተካ ሚና አላቸው ነው ያሉት።
ተቋማቱም የገጠማቸውን ችግር ተቋቁመው ባለፉት አራት ዓመታት ከቅድመ መደበኛ አስከ ዲግሪ ያሉ 8 ሺህ 800 መምህራንን አሠልጥነዋል፤ ለማስመረቅም በዝግጅት ላይ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ዓመትም ከ5 ሺህ በላይ ሠልጣኞችን በአስሩም ኮሌጆች እንዲገቡ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
ተቋማቱ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ብቁ መምህራንን በማሠልጠን፣ የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናት እና ምርምሮችን በማድረግ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወናቸውን አብራርተዋል።
በሥራ ላይ ያሉ መምህራንን አቅም ለማጎልበትም በ2017 ዓ.ም የተሰጠው ሥልጠና መምህራኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እንዲተጉም አስችሏል ነው ያሉት።
ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ግምገማ የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በጋራ በሚሠሩበት ሠነድ ላይ በመፈራረም የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
ዘጋቢ፦አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!