የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል በአካባቢው ውጤታማ ሥራ እየሠራ ነው።

5

ሰቆጣ: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዝናብ አጠር አካባቢዎች የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን እና የተዳቀሉ እንሰሳትን ለአርሶ አደሮች የማላመድ ተግባር የሚከውን የምርምር ማዕከል ነው።

ማዕከሉም በተያዘው የምርት ዘመን በእንቁ ዳጉሳ፣ በማሾ፣ በመልካም ማሽላ፣ በቁንጮ ጤፍ እና በስንዴ ዘር ላይ ሰፊ ሥራ ሠርቷል።

አርሶ አደር መለሰ ግርማይ የሰቆጣ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ከምርምር ማዕከሉ ያገኙትን የ”መልካም ማሽላ” ዘርን በኩታገጠም አልምተዋል።

የአካባቢው ማሽላ በግንቦት ተዘርቶ በታኅሣሥ የሚደርስ አድካሚ ዘር እንደነበረ የሚያስታውሱት አርሶ አደር መለሰ በምርምር ማዕከሉ ያገኙት መልካም ማሽላ ሐምሌ አጋማሽ ተዘርቶ በጥቅምት የሚደርስ ፈጣን ዘር ነው ብለዋል።

ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በኩታገጠም በ”መልካም ማሽላ” የዘሩት አርሶ አደሩ በሄክታር እስከ 15 ኩንታል እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል።

የቁንጮ ጤፍን በኩታገጠም በማልማታቸው ተጠቃሚ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጻግቭጅ ወረዳው አርሶ አደር ወልደሥላስ ግርማይ ናቸው።

የቁንጮ ጤፍ በአጭር ጊዜ የሚደርስ እና የምርት አያያዙ የሚያምር፣ ለአካባቢው ተስማሚ መኾኑንም ገልጸዋል።

የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪ አደመ ምህረቱ ሥነ ምህዳርን መሠረት ያደረገ ምርጥ ዘር እና ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሮች እያስፋፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በጻግቭጅ ወረዳ 10 ሄክታር የጤፍ ኩታገጠም እና በሰቆጣ ወረዳ የአምስት ሄክታር የ”መልካም ማሽላ” ኩታገጠም መሬት ከግብርና መምሪያ ጋር በመነጋገር እንደደገፉ ገልጸዋል። ተመራማሪው በዚህም ከ50 በላይ አርሶ አደሮችን ይዘው እየደገፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የምርምር ማዕከሉ ለግብርናው የጀርባ አጥንት ነው ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት በማሾ እና በእንቁ ዳጉሳ የተመዘገበው የምርት መጠን አበረታች እንደኾነ ጠቁመዋል። በወይንአደጋ አካባቢዎችም የተመረጡ የጤፍ፣ የማሽላ፣ የስንዴ እና የባቄላ ዘርን ለአርሶአደሮች በነጻ በማከፋፈል የሚታይ እና የሚጨበጥ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል።

በቀጣይም በምርምር ማዕከሉ የቀረበ ምርጥ ዘርን ለሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ ከወዲሁ ምርጥ ዘርን በመሠብሠብ የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በምርምር ማዕከሉ የተደገፉ የአርሶ አደር ማሳዎች ተጎብኝተዋል።

ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመድኃኒት አቅርቦትን በማሻሻል የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የትኩረት አቅጣጫ ነው።
Next articleየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትምህርት ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቀልበስ የማይተካ ሚና አላቸው።