
አዲስ አበባ: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ1939 ዓ.ም የተመሠረተው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሕክምና መድኃኒቶችን ገዝቶ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ማድረግ ዋናው ተግባሩ ነው።
ጥራት ያለው፣ ፈውስ የሚኾን እና ደኅንነት ያለውን መድኃኒት በጊዜ እና በፍትሐዊነት ማድረሱን ይቀጥል ዘንድ በተቋሙ በየዓመቱ ጉባዔ ይካሄዳል። ዘንድሮም ሰባተኛውን የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ ጉባኤ አካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስቴር አንዱ የማሻሻያ ተግባር የመድኃኒት አቅርቦትን ማሻሻል መኾኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ደግሞ ለዚህ ማሻሻያ እውን መኾን የላቀ ባለድርሻ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የተሠራው የመድኃኒት ግዥ እና አቅርቦት አሠራር አዋጅ መሻሻል የነበረውን ውጣ ውረድ እና ቢሮክራሲ በመቀነስ በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ አግዟል ብለዋል።
የዚህ ዓመት ትኩረት ደግሞ መድኃኒትን በብዛት እና በጥራት ማቅረብ አሠራሩንም ዲጂታላይዝድ በማድረግ ተደራሽነቱን እና የማኅበረሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መኾኑን ነው ያነሱት።
የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን ከማጠናከር ጎን ለጎን ደግሞ የሚመረተው መድኃኒት ፈዋሽነት እና ጥራትን ማረጋገጥም ሌላኛው የትኩረት ነጥብ ይኾናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ተቋሙ ባለፈው ዓመት ከ68 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒት ገዝቶ ለተጠቃሚ ማቅረብ መቻሉን አንስተዋል። ከዚህ መካከልም ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነው ለተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ተደራሽ የኾነ ነው ብለዋል።
አማራ ክልልን ጨምሮ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎችም በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ውስጥ ኾኖ ተቋሙ መድኃኒት ተደራሽ ለማድረግ ጥረት አድርጓል ነው ያሉት።
ተቋሙ በቀጣይ የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከር ዲጂታል አሠራርን በስፋት መተግበር፣ ከሀገር ውስጥ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት፣ የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ጋር በቅርበት መሥራት እና አዲስ የግዥ ሥርዓትን መገንባት ላይ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
ጥራት ያለውን መድኃኒት በጥራት እና በፍጥነት ማድረስም የአገልግሎት ተቋሙ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ኾኖ ይቀጥላል ብለዋል። በጉባኤው በዓመቱ የላቀ አፈጻጻም የነበራቸው ባለድርሻ ተቋማትም ዕውቅና ተሰጧቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን