የቻግኒ የዳልጋ ከብት ብዜትና ዝርያ ማሻሻያ በገንዘብ ችግር ምክንያት ተገቢውን ጥቅም መስጠት እንዳልቻለ ማዕከሉ አስታወቀ፡፡

800

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) በዓመት ከ750 በላይ ጊደር ብቻ የሚያስገኝ ሀብት ቢሆንም ትኩረት በማጣቱ ያሉት ክልስ ጊደሮች፣ ክልስ ወይፈኖችና ንጹሕ የፎገራ ወይፈኖች ተደምረው ከ150 አይበልጡም፡፡

የቻግኒ የዳልጋ ከብት ብዜት እና ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል በ1978 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመው የፎገራ ከብት ዝርያን ጠብቆ ለማቆየት፣ ለማሻሻል፣ የተሻሻለ የከብቶች ዝርያ ለማኅበረሰቡ ለማድረስ እና የመኖ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ነበር፡፡ የፎገራ ከብት ዝርያን መጠበቅ ያስፈለገውም በቀላሉ አካባቢን ስለሚላመዱ፣ ከፍተኛ የሥጋ እና የወተት ምርት ስለሚያስገኙና ለእርሻ ተመራጭ ስለሆኑ ነው፡፡ የማዕከሉ ዳይሬክተር ፈንታሁን ዳኘው እንዳሉት ማዕከሉ ንጹሕ የፎገራ የከብት ዝርያን ጠብቆ በማቆየት ብቸኛው ነው፡፡ በውስጡ ከሚገኙ 1 ሺህ 409 ከብቶች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ንጹሕ የፎገራ ዝርያ፣ ቀሪዎቹ ክልሶች ናቸው፡፡

ማዕከሉ የተቋቋመው በቂ ቁሳቁስ ተሟልቶ ስለነበር ለማኅበረሰቡ ክልስ ወይፈኖችን፣ ንጹሕ የፎገራ ወይፈኖችን እና ክልስ ጊደሮችን በጥሩ ሁኔታ ሲያሰራጭ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ቁሳቁሶቹ ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ተከከትሎ ማዕከሉ በሚጠበቅበት ልክ ግልጋሎት እየሰጠ አለመሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

Image may contain: sky, outdoor and nature

ንጹሕ የፎግራ ከብት ዝርያ፣ ትላልቅ ወንዞች፣ በቂ ቦታ እና የሰው ኃይል መኖር መልካም አጋጣሚ ናቸው፡፡ ያሉትን ከብቶች በመጠቀም በዓመት ከ750 በላይ ክልስ ጊደር ብቻ ለኅብረተሰቡ ማድረስ ይቻል ነበር፡፡ አሁን ግን ክልስ ወይፈን፣ ክልስ ጊደር እና ንጹሕ የፎገራ ወይፈኖች ተደምረው ከ150 መብለጥ አልቻሉም፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ወንዙን ገድቦ በበቂ ሁኔታ መኖ ለማዘጋጀት፣ የመኖ ማጨጂያ እና ማዘጋጃ ቤለር፣ ትራክተር፣ ከብቶችን ለማከም የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች በበጀት ችግር አልተሟሉም፡፡ የከብቶች ሰውነት መጎሳቆሉን፣ በረት አለመኖሩን፣ በቂ መኖ አለመኖሩን እና በጥሩ ሁኔታ አለመቀመጡን አብመድ በቦታው ተገኝቶ ታዝቧል፡፡ ማዕከሉ ዙሪያው ባለመታጠሩ ከአርሶ አደር ከብቶች ጋር ተቀላቅለውም ይውላሉ፤ ይህም የዝርያ መበከል እንደሚያስከትል አብመድ ተረድቷል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለማዕከሉ በቂ ትኩረት ባለመስጠቱ በሚገባው ልክ ጥቅም እያስገኘ አለመሆኑን ደግሞ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው፤ በቂ ገንዘብ በመመደብ ማዕከሉን ማጠናከር እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

Image may contain: outdoor and nature

የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጄንሲም ችግሩ ከአቅሙ በላይ ሆኖ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ ኤጄንሲው ለማዕከሉ የበጀት እና የሙያ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም የሚሰጠውን ጥቅም ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ውሳኔ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡ በኤጄንሲው የማዕከላት ክትትል ባለሙያ ክንዴነህ የማታው እንዳሉት ችግሮቹን ለመፍታት ከፍተኛ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ ማዕከሉ የውስጥ ገቢን መጠቀም ከቻለ ችግሩን ማቃለል እንደሚቻል በመግለጽም ኤጄንሲው የውስጥ ገቢ አጠቃቀም መመሪያ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በአዋጅ የተቋቋመው በመንግሥት በጀት ብቻ እንዲተዳደር በመሆኑ የውስጥ ገቢን ለመጠቀም አዋጁን በአዋጅ መተካት እንደሚያስፈልገውም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ኤጄንሲው ጉዳዩን ለክልል ምክር ቤት ማሳወቁንና ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ስድስት ማዕከላት፣ ሁለት ቤተ ሙከራ እና የጤና ማዕከላት አሉ፡፡ የክልሉን የእንስሳት ሀብት ለመስፋፋት ምቹ ሁኔታ ቢሆኑም ባለመጠናከራቸው ምክንያት ጥቅም እየሰጡ አለመሆኑን ግን ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡ ምናልባትም መመሪያው ጸድቆ የውስጥ ገቢያቸውን መጠቀም የሚችሉ ከሆነ ማዕከላቱ ጥሩ አገልግሎት እንደሚሰጡ ነው ባለሙያው ያስታወቁት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleዛሬ በመላው ዓለም የሚኖሩ እና የሚሊዮኖችን ሕይወት ከሞት አፋፍ የታደጉ ሰዎች የሚመሠገኑበት ቀን ነው፡፡
Next articleየሦስትዮሽ ድርድሩ ትናንትም ቀጥሎ መካሄዱን ሚኒስቴሩ አስታወቀ።