
ወልድያ: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት የገቢ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች የገቢ ዕቅዱን ለማሳካት የቅንጅት ሥራ ይጠይቃል ብለዋል። ለገቢ ዕቅዱም በየቦታው በሚሠራው ሥራ በትብብር ለመሥራት ቁርጠኝነት እንዳለ ነው የገለጹት።
የከተማ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ሞገስ አስማማው በ2018 በጀት ዓመት 1ቢሊዮን 152 ሚሊዮን 581 ሺህ ብር ለመሠብሠብ መታቀዱን ተናግረዋል።
በአንደኛው ሩብ ዓመትም 237 ሚሊዮን ብር በመሠብሠብ የዕቅዱን 21 በመቶ በመፈጸም መልካም ጅምር ላይ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
ወደ ንግድ መረቡ ያልገቡ ነጋዴዎችን ወደ መስመር በማስገባት ሁሉንም የገቢ አማራጮች አሟጦ ለመጠቀም ታቅዷል ነው ያሉት።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አስናቀች ኃይሌ የገቢ ተቋሙ አብዮት ፈጥሮ የ2018 ክንውንን ከዕቅድ በላይ መፈጸም ይጠበቅበታል ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ንጉሥ ዝናቡ ገቢ መሠብሠብ የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
የተጀመሩ ልማቶችን ለማጠናቀቅ እና አዳዲስ ልማቶችን ለመጀመር ገቢ መሠብሠብ ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመድረኩ በ2017 በጀት ዓመት መልካም የግብር አፈጻጸም ለነበራቸው ግለሰቦች እና በገቢ አሠባሠባቸው የተሻለ ለፈጸሙ ክፍለ ከተሞች ዕውቅና ተሰጥቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!