ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መርቀው ሥራ አስጀመሩ።

3

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 08/2018(አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ማለዳ በባሌ ዞን፣ ደሎ መና ወረዳ በመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አማካኝነት የተጀመረውን የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መርቀናል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የወልመል ወንዝን በመስኖ በሚገባ በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን በማላቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተከናወነ ነው። ፕሮጀክቱ ዘላቂ የገጸምድር የመስኖ ሥርዓት በመገንባት የግብርና ሥራው ለዘመናት በዝናብ ውኃ ላይ ተመስርቶ የነበረውን የአካባቢውን ሕዝብ ዘላቂ የኑሮ ዘዴ ለማጎናፀፍ ታልሞ ተከናውኗል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር በሚገባበት ወቅት 20 ሺህ 000 ለሚሆኑ አርሶአደሮች ለሚያገለግል 9 ሺህ 687 ነጥብ 45 ሄክታር የእርሻ መሬት አስተማማኝ የመስኖ አቅርቦት ይኖረዋል። ይኽም የግብርና ምርታማነትን የሚያሳደግ፣ ለድርቅ የማይበገር ከባቢን የሚፈጥር ብሎም በማኅበረሰቡ አዳዲስ የሥራ እድል የሚፈጥር ይኾናል ብለዋል።

ከነዚህ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ባሻገር የአካባቢውን የውኃ አሥተዳደር ተቋማትን በማጠናከር፣ የአካባቢውን ሕዝብ ባለቤትነት በማሳደግ ብሎም የወልወልን ወንዝ ዘላቂ አጠቃቀም በማጎልበት የተሻለ የምግብ ሉዓላዊነት ጠቀሜታ ያገለግላል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመጻሕፍት አቅርቦት ዝግጅት ተጠናቅቋል” ትምህርት ቢሮ
Next articleከ1ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ ዐቅዶ እየሠራ መኾኑን የወልድያ ከተማ ሥተዳደር አስታወቀ።