“ዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሻገር እና የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ቁልፍ ተቋም ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ.ር)

4

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በቀጣይ መሥራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ መቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት ክልሉ ያለውን ሀብት በመለየት፣ በማወቅ እና ለትውልድ የሚተርፍ ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት ግብ በመያዙ ነው ብለዋል።

ተቋሙ የባለቤትነት፣ የቁጥጥር እና ገቢ የማመንጨት ዓላማ ያለው መኾኑንም ገልጸዋል። ሁለንተናዊ ልማት እና ብልጽግናን በማፋጠን የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ አንገብጋቢ የኾነውን የልማት ፋይናንስ ማነቆዎችን ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ሆልዲንጉ ከአሁን በፊት በክልሉ መንግሥት ተቋቁመው የቆዩ እና ለወደፊት የሚቋቋሙ ድርጅቶችን በባለቤትነት ይዞ የሚመራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ይህም የሃብት ብክነትን፣ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን እና የኀላፊነት መደራረብን በማስቀረት የመንግሥትን እና የሕዝብ ሃብቶችን በአግባቡ ለመምራት እንደሚያስችል አመላክተዋል።

የተቋቋመው የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት ኢንቨስትመንትን ያመጣል፤ ለክልሉ ተጨማሪ ሀብት ይፈጥራል ብለዋል። የመንግሥት እና የሕዝብ የኾኑ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ሃብቶችን በንግድ መርሕ ብቻ እንዲመራ ያደርጋል ነው ያሉት።

ዘመናዊ የኮርፖሬት እና የፋይናንስ አሠራርን በመዘርጋት በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚያጋጥሙ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን እንደሚፈታም አንስተዋል።

ተቋሙ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሻገር እና የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ቁልፍ ተቋም ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው የገለጹት።

የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታደሰ ካሳ (ዶ.ር) በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች እና አደረጃጀቶች ተቋቁመው ሲሠሩ የቆዩትን የመንግሥት እና የሕዝብ ድርጅቶችን በአንድ ለመምራት የተቋቋመ ድርጅት መኾኑን ጠቁመዋል።

ከአሁን በፊት በተለያዩ አደረጃጀቶች የቆዩ ድርጅቶች የተለያየ አፈጻጸም ደረጃ ያላቸው መኾናቸውን ጠቁመዋል። ሆልዲንጉ በቀጣይ እነዚህን ድርጅቶች በመምራት ውጤታማ ሥራ በመሥራት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።

በኢንቨስትመንት እና በንግድ ዘርፍ እየሠሩ ያሉትን ድርጅቶች አቀናጅቶ ትርፋማ እንዲኾኑ ለማድረግ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ወደ ዘመናዊ አሥተዳደር ሥርዓት ማስገባት እና በክልሉ ያለውን የዕድገት ፍላጎት ሊያሳካ የሚችል ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጣና ፎረም ከጥቅምት14/2018 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳል።
Next article“የመጻሕፍት አቅርቦት ዝግጅት ተጠናቅቋል” ትምህርት ቢሮ