
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 08/2018 (አሚኮ) አፍሪካ በዓለም የፖለቲካ ሥርዓት የሚገባትን ስፍራ እንድትይዝ ለማድረግ ያለመው የዚህ ዓመት የጣና ፎረም በሁለት ከተሞች ይካሄዳል።
የጣና ፎረምን ዝግጅት አስመልክቶ አዘጋጆቹ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫውም የጣና ፎረም ዘንድሮ ከጥቅምት 14 /2018 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሏል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ በባሕር ዳሩ መድረክ ሁለት ሁነቶች እንዳሉ ገልጸዋል። በዚህም የአፍሪካ ቀንድ ላይ ያሉ የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ልዩ መልዕክተኞች በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ይመክራሉ ብለዋል።
ይህ መድረክም ሌሎች አካላት ቀጣናውን እንዴት እንደሚመለከቱት ለማወቅ እና ለቀጣናው የሰላም መፍትሔ ለማምጣት ጠቃሚ መኾኑን አንስተዋል።
በባሕርዳር ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአህጉሪቱ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ይመክራሉ ነው የተባለው። መንግሥትም ይህንን ፎረም ለማካሄድ የደኅንነት እና ሌሎች በቂ ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት።
ፎረሙ በዋናነት በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት ውስጥ አፍሪካ ሊኖራት የሚገባውን ቦታ ለማስጠበቅ መሠረት አድርጎ ይመክራል ብለዋል። አፍሪካም በተቀመጠላት አቅጣጫ ብቻ ሳይኾን ራሷም በአቅጣጫ ዘዋሪ ልትሆንበት በምትችል ነጥቦች ይመክራል ነው ያሉት።
የባሕር ላይ ደኀንነት እና የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ በመኾኑ በዚህ ጉዳይ ላይም እንደሚመክር አንስተዋል።
ኢትዮጵያም የቀጣናውን የባሕር ደኅንነት ላይ ከራሷ ጥቅም ባለፈ የማስከበር ኃላፊት ያለባት መኾኑን በፎረሙ ላይ በቂ ግንዛቤ ይፈጠራል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!