“የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ኾኖ ቀጥሏል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

3

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የባሌ ዞን የመጀመሪያ ቀን ጉብኝት ያሳየን በድንቅ ተፈጥሮ እና በልማት ሥራ እድገት መካከል ያለውን መስተጋብር ነው ብለዋል።

በአስደናቂ ብዝኅ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ኾኖ ቀጥሏል። ይኽ እምቅ አቅም በፓርኩ እምብርት ላይ የተገነባው የዲንሾ ሎጅ በቅርቡ ሲጠናቀቅ የበለጠ ይጠናከራል ነው ያሉት። በአቅራቢያው በመገንባት ላይ ያለውና በቅርቡ የሚጠናቀቀው የሶፍኡመር ሎጅ ቱሪዝምን የኢኮኖሚያችን ቁልፍ መሪ አድርጎ ያስቀመጠው የኢትዮጵያን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የሚተገብር ነው። ሎጁ በሶፍኡመር ዋሻ የጎብኝዎችን ቆይታ ከፍ የሚያደርጉ እና የመዝናኛ አገልግሎት መስጫዎች በሶፍኡመር ዋሻ ልማት ፕሮጀክት እገዛ የሚዘጋጁበት መኾኑን ገልጸዋል።

በመንገድ መሠረተ ልማት ረገድ የሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መንገድ የማሻሻያ ፕሮጀክት ከፍተኛ አምራች የሆኑትን የምሥራቅ ባሌ እና የባሌ ዞኖችን ምርታቸውን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚያገናኝ ነው። ይኽ መሥመር ተደራሽነትን እና የኢኮኖሚ ተያያዥነትን ብቻ ሳይሆን እንደሶፍኡመር ዋሻ እና የባሌ ተራሮች ወደ መሰሉት ዐበይት የመስኅብ ሥፍራዎች ጉዞን የሚያሳልጡ ናቸው ብለዋል።

ድርብ አስፋልት ንጣፍ ባለው ከፍ ያለ ደረጃ የተገነባው መንገድ 29 ኪሎሜትር የከተማ እና የገጠር መንገድን የሚያካትት፣ ከ12 እስከ 140 ሜትር ርዝመት ያላቸው አምስት ድልድዮች የተሠሩበት መኾኑንም ገልጸዋል።

የቀኑን ጉብኝታችንን የወይብ ወንዝ የጎርፍ መቆጣጠሪያ ፕሮጀክትን በመመልከት አጠናቅቀናል። ፕሮጀክቱ በሶፍኡመር ዋሻ የሚጓዘውን የወንዙን የውኃ ፍሰት በመቆጣጠር ዓመቱን ሙሉ ወደ ዋሻው የሚደረግ ጉዞ እንዳይስተጓጎል ለማድረግ እና የዋሻውን ሥነምኅዳር ለመጠበቅ ታልሞ የተሠራ ነው። ሁሉም ሥራዎች ቀጣይነት ላለው ልማት ያለንን ጽኑ አቋም እና ተግባር የሚገልጡ ናቸው ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleፍትሐዊ የኾነውን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጎረቤት ሀገራት ሊደግፉት ይገባል።
Next articleችግሮችን በመነጋገር መፍታት እና ሰላምን መጠበቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች ማኅበር ጠየቀ።