
አዲስ አበባ: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የጠየቀችው የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ መኾኑን ጎረቤት ሀገራት በውል መረዳት እና መተባበር እንደሚገባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ለማስመለስ የተጀመረው ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ዳር ይደርስ ዘንድ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በንቃት ሊሳተፉ ይገባልም ብለዋል።
የባሕር በር ባለቤት የመኾን ጉዳይ በየትኛውም መስፈርት ሲለካ የሀገር እና የሕዝብን ሕልውና መሠረት ያደረገ ጥያቄ በመኾኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚስማሙበት ጉዳይ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ከቀይ ባሕር በ60 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ትናንት የባሕር በር ባለቤት የነበረች ቢኾንም በታሪክ አጋጣሚ ሃብቷን ተነጥቃ የበይ ተመልካች እንድትኾን ተደርጋ ቆይታለች ነው ያሉት።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱ ባልተገባ መንገድ ያጣችውን ሃብቷን ለማስመለስ ጠንካራ አቋም በመያዝ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በድህነት ውስጥ የመኖሯ አንዱ እና መሠረታዊው ምክንያት የባሕር በር አልባ መኾኗ እንደኾነም ተናግረዋል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተይዞ ያለ ባሕር በር መኖር የሚያደርሰው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እየጠየቀችው ያለው ትናንት የራሷ የነበረን ሃብት በመኾኑ ስለ ፍትሐዊ ጥያቄዋ ጎረቤት ሀገራትም ጉዳዩን በውል መረዳት እና መተባበር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የልማት ብቻ ሳይኾን የሕልውና ጉዳይ የኾነውን የባሕር በር ለማግኘት ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በኾነ መንገድ ጥረት እያደረች ትቀጥላለች ብለዋል። የተጀመረው መንገድ ውጤታማ ይኾን ዘንድ ኢትዮጵያውያን የውስጥ አንድነታችን ከመቼዉም ጊዜ በላይ ማጠንከር ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅም ላይ ልዩነት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፤ አንድነት እና ትብብር መርሕ ኾነው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!