“የምገባ መርሐ ግብሩ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ፍላጎታቸውን ጨምሯል” የተማሪ ወላጆች ‎

5

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ወይዘሮ ጎጃም ታደለ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በሽምብጥ ትምህርት ቤት የሚማረው ልጃቸው የምገባ ተጠቃሚ እንደነበር ነግረውናል፡፡

ወላጇ “የምገባ ፕሮግራም ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ፍላጎታቸውን ጨምሯል” ነው ያሉት፡፡

‎በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ ጥሩ ለውጥ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ሕጻናት ቤት ላይ በቀላሉ የማያገኙትን ወተት እንዲያገኙ አድረጓል ብለዋል።

‎ልጆቻቸው በቁልቋል ሜዳ ትምህርት ቤት የሚማሩት አቶ በለጠ ቢሻው የወላጆች እና መምህራን ኅብረት ኮሚቴ አባል ናቸው።

‎በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎች በኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ የኾኑ ነዋሪዎች ልጆች መኾናቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ልጆቻቸው የተማሪዎች ምገባ ተጠቃሚ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ ምገባው ለተማሪዎችም ኾነ ለወላጆች እፎይታን የሰጠ እንደኾነ ነው የተናገሩት። ምገባው እንዲቀጥል ወላጆች እየጠየቁ ነው።

‎የሽምብጥ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ጋሻው ጥሩነህ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ለመማር ማስተማሩ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የምግብ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ተማሪዎች አሉ፤ ምገባው ይህንን ችግር ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት፡፡ ለልጆች አካላዊ እና አዕምሯዊ እድገት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የምገባ ፕሮግራሙ ለቅድመ መደበኛ እና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ከ600 በላይ ተማሪዎች ሲሰጥ እንደቆየም ተናግረዋል፡፡

‎የተማሪዎችን ውጤት በአንድ ዓመት ለመገምገም አስቸጋሪ ቢኾንም ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንቃት ይሳተፋሉ። ‎በዚህ ዓመት የሚመገቡ ተማሪዎችን ቁጥር ጨምሮ ለማስቀጠል በዕቅድ ተይዞ ከኅብረተሰቡ ሃብት የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

ተቋማት፣ ባለሃብቶች እና ረጂ ድርጅቶች ሕጻናትን ለመመገብ እንዲተባበሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

‎የቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አገር ነቃ ጥበብ በትምህርት ቤቱ ባለፈው ዓመት የተጠናከረ የምገባ ፕሮግራም እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ የተለያዩ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስልቶችን ተጠቅሞ ሁሉንም ተማሪዎች ማለትም ለ1 ሺህ 736 ተማሪዎች ሲመግብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ምገባው የተማሪ ቁጥር መቀነስን፣ ማቋረጥን፣ የመቅረት እና ማርፈድ ችግሮችን ማስቀረቱንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ምገባው ገና እንዳልጀመረም ርእሰ መምህሯ ተናግረዋል።


‎የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተጀመረ ነው ብለዋል። ምገባውም የተማሪዎችን ከትምህርት ማርፈድ እና መቅረትን ቀርፏል፤ የመማር ተነሳሽነት መጨመሩንም አንስተዋል፡፡

‎ባለፈው ዓመት በ17 ትምህርት ቤቶች 20 ሚሊዮን ብር መንግሥት መድቦ 9 ሺህ 267 ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ማግኘታቸውን አንስተዋል፡፡

‎በዚህ ዓመት የተማሪዎችን ምገባ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።

‎በመንግሥት ትምህርት ቤቶች 20 ሺህ ተማሪዎችን ለመመገብ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡ ምገባው ለቅድመ መደበኛ እና ልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ የበጀት ድጋፍ ከተገኘ ሌሎች ተማሪዎችንም ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

‎‎የዚህ ዓመት ትምህርት ጀምሯል ያሉት ኀላፊው ምገባውም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቃቸው በቅርቡ እንደሚጀመር ነው የገለጹት፡፡

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተገልጋዮችን ለምሬት የሚዳርጉ ብልሹ አሠራሮችን በበቂ ሁኔታ መፍታት ይገባል።
Next articleበምዕራብ ጎንደር ዞን ያለውን ፀጋ ለማልማት ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።