ዛሬ በመላው ዓለም የሚኖሩ እና የሚሊዮኖችን ሕይወት ከሞት አፋፍ የታደጉ ሰዎች የሚመሠገኑበት ቀን ነው፡፡

135

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) በየዓመቱ ሰኔ 7 የደም ለጋሾች ቀን በዓለማቀፍ ደረጃ ተከብሮ ይውላል፡፡

የነፍሰጡሮችን ስቃይ ዓይተው በዝምታ ማለፍ ያልቻሉ ትሁቶች፣ የእናቶችን ሕመም አብዝተው የታመሙ አዛኞች፣ በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዳ ተርበትብተው፣ ከመኪና አደጋ በተአምር ተርፈው በሞት እና በሕይወት መካከል የሚያጣጥሩ ወገኖችን ስሜት ተጋርተው ደማቸውን ያለስስት የለገሱ ሁሉ በየዓመቱ በዚህ ቀን ስለበጎነታቸው ይመሠገናሉ፡፡

እንደዓለም ጤና ድርጅት እሳቤ ደግሞ ምሥጋናው እልፎችን ከደም ለጋሾች ጎን ለማሰለፍ እና ዕውቅና ለመፍጠር ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት የዓለም ደም ለጋሾች ቀንን በባሕር ዳር ከተማም በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷል፡፡ ‘‘የዘንድሮውን የደም ለጋሾች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት አስቸጋሪ አድርጎብናል’’ ያሉት የባሕር ዳር ደም ባንክ ኃላፊ ምክሩ ሺፈራው ቀኑ ታስቦ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

የዓለም ደም ለጋሾች የምሥጋና ቀንን ታሳቢ አድርገው ደም መለገስ ለሚፈልጉ ወገኖች ደግሞ ከቀድሞው የግዮን ሆቴል ወደ ሙሉዓለም የባህል ማዕከል በሚወስደው መንገድ ላይ በጎ ፈቃደኞች ደም እንደሚያሰባስቡ ተናግረዋል፤ ደም በመለገስ የምሥጋናው አካል እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ዝግጅት እንደሚኖርም አስታውቀዋል፡፡

ለ25 ሆስፒታሎች ደም የሚያቀርበው የባሕር ዳር ደም ባንክ በ2012 ዓ.ም 12 ሺህ ከረጢት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ እስካሁን ወደ 18 ሺህ ከረጢት ደም ተስብስቧል፡፡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በአማራ ክልል የሚገኙ የእግር ኳስ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ለጋሽ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የደም ባንኩ ሠራተኞች ላበረከቱት አስተዋፅዖም ኃላፊው ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በመጭው ጥር ይጀምራል፡፡
Next articleየቻግኒ የዳልጋ ከብት ብዜትና ዝርያ ማሻሻያ በገንዘብ ችግር ምክንያት ተገቢውን ጥቅም መስጠት እንዳልቻለ ማዕከሉ አስታወቀ፡፡