ተገልጋዮችን ለምሬት የሚዳርጉ ብልሹ አሠራሮችን በበቂ ሁኔታ መፍታት ይገባል።

11

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 13ኛ ዓመት፣ 47ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

የከተማ አሥተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መንግሥቱ ቤተ በፈጣን ለውጥ እና ዕድገት ላይ የምትገኘውን የደብረ ብርሃን ከተማ በኮሪደር ልማት፣ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች፣ በሰው ተኮር ልማት ተግባራት እና በማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል በኩል ባለፉት ጊዜያት አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

የጤና ተቋማት ግብዓት በማሟላት እና ርካታን የሚጨምር የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ማሳያ የሚኾኑ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ደብረ ብርሃን ያላትን ጸጋ በመጠቀም በከተማ ግብርና ልማት ዘርፍም ያለው እንቅስቃሴ ለውጥ የተመዘገበበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ተገልጋዮችን ለምሬት የሚዳርጉ ብልሹ አሠራሮችን በበቂ ሁኔታ መታገል፣ አስተማሪ ደንብ የማስከበር ሥራዎች መሥራት፣ በደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ማስያዝ እና የጋራ ተልዕኮዎችን በወጥነት መወጣት ላይ በቀጣይ የበለጠ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የበጀት ዓመቱን ዋና ዋና እቅዶች ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፣ የማምረት አቅም እንዲያድግ እና የአንድ መሶብ አገልግሎት በማስጀመር ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ላይ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን መቻል፣ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት፣ ቴክኖሎጂ መር ግብርናን በማከናወን የምርት ብክነትን ለመቀነስ ብርቱ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።

በከተማዋ የመስህብ ሀብቶችን በመለየት፣ በማስተዋወቅ እና በማልማት የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሰደግ በበጀት ዓመቱ ሌላኛው ትኩረት የተሰጠው ተግባር መኾኑን አስንተዋል፡፡

አካታች የሥራ እድል ፈጠራን በመተግበር የዜጎችን ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሠራል ብለዋል፡፡

የጤና ተቋማትን አቅም ማሳደግ፣ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ ተግባራት የበጀት ዓመቱ እቅድ አካል መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘላቂ የገቢ አቅም በማሳደግ እና የበጀት አሥተዳደር ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀም ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

የላቀ የፍትሕ ተደራሽነትን ማሳደግ፣ የዳኝነት እና የፍትሕ ነጻነት ማስጠበቅ እና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ በትኩረት የሚሠራባቸው ነጥቦች መኾናቸው ተጠቅሷል፡፡

ምክር ቤቱ የከተማ አሥተዳደሩ በጀት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በባሌ ዞን በመገንባት ላይ ያለውን የዲንሾ ሎጅ እና የጌሴ የሳርምድርን ጎበኙ።
Next article“የምገባ መርሐ ግብሩ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ፍላጎታቸውን ጨምሯል” የተማሪ ወላጆች ‎