
አዲስ አበባ: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በደብረ ብርሃን ከተማ በግለሰቦች የተሠራ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
አሜሪካዊቷ አንጀሊክ ኪድስሚ የተባሉ ግለሰብ ከራሳቸው እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በደብረ ብርሃን ከተማ አጼ ዘረያዕቆብ ክፍለ ከተማ ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ወጋገን የመጀመሪያ ትምህርት ቤት መሠረት የተጣለው በ2010 ዓ.ም ሲኾን ትምህርት ቤቱ ምቹ እና ጽዱ የመማሪያ ክፍሎች እና ቅጥረ ግቢ እንዲኖረው ተደርጎ ተገንብቷል። ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ 480 በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ የሚገኝ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ነው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ ባለፉት ሦሥት ወራት በከተማ አሥተዳደሩ ወደ 49 ሚሊዮን ብር በማኅበረሰብ ድጋፍ እና አጋር አካላት ወጭ ተደርጎ 36 የመማሪያ ክፍሎች መሠራታቸውን አንስተዋል።
የወጋገን ትምህርት ቤት ከእነዚህ ልዩ የሚያደርገው በግለሰቦች መልካም ፈቃድ የተገነባ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ በማድረግ የተገነባ የሰብዓዊነት ጥግ ማሳያ መኾኑ እንደኾነ ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ትምህርት ቤቱ ለሌሎች ከተሞች ሞዴል የኾነ እና በግቢው ውስጥ የሕጻናት መጫዎቻዎች፣ ስፖርታዊ ማዘውተሪያዎች፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት እና መሰል የተማሪዎችን ክህሎት የሚያዳብሩ ሥራዎች የተሟሉለት ነው ብለዋል።
የወጋገን ትምህርት ቤትን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ትምህርት ቤቱ የሰውን ልጅ ሰብዓዊነት፣ ሩህሩህነት እና የማኅበረሰብ ችግር መፍትሄ ፍለጋ የሚዋትቱ የዕውቀት ባለቤቶች እንዳሉ ማሳያ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን በንድፈ ሃሳብ ከማስተማር ባለፈ የተለያዩ የሕይወት ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ የሚያስችሉ የግብርና ሥራዎች እና መዝናኛዎች የተሟሉለት መኾኑ ትምህርት ቤቱ በክልል ደረጃ ሞዴል የሚኾን እንደኾነም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፦ አደራው ምንውዬለት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን