የጎንደር ከተማ ምክር ቤት አባላት በከተማዋ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ተመለከቱ።

2

ጎንደር: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ምክር ቤት አባላት የአይራ የሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከልን፣ በኮሪደር ልማቱ ተነሽ የኾኑ የንግዱ ማኅበረሰብን መልሶ ለማደራጀት እየተሠሩ ያሉ የንግድ ሸዶችን፣ በ55 ሚሊዮን ብር የተገነባውን የምገባ ማዕከል እንዲሁም እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማቶችን ጎብኝተዋል።

የአይራ ሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል መገንባቱ ሸማቾች ማኅበረሰቡን ያማከለ እና የሚፈልገውን ጥሬ ዕቃ በቀጥታ ኑሮውን ባማከለ ደረጃ መገበያየት የሚችልበትን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን በጉብኝታቸው መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

ሸማቹ ማኅበረሰብ በትራንስፖርት ምክንያት እንዳይቸገር ዘመናዊ ባስ በመዘጋጀት ላይ እንደኾነም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላሸት ገልጸዋል።

የገበያ ማዕከሉ 6ሺህ 200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እና በ160 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባ እንደኾነም ተገልጿል። አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጠ እንደኾነም የምክር ቤት አባላቱ በጉብኝቱ ማረጋገጥ ችለዋል።

በጎንደር ከተማ በኮሪደር ልማት እና በተለያዩ የበጀት ምንጮች እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ውበት ከመጨመራቸው በሻገር የነዋሪዎችን የመልማት ዕድል በሚያሳድግ መልኩ እየተከወኑ መኾኑን በመስክ ምልከታ መታዘባቸውን የምክር ቤት አባላቱ ሃሳብ ሰጥተዋል።

የጎንደር ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ የጀመረ ሲኾን ከጥቅምት 07 እስከ 09/2018 ዓ.ም ይቆያል።

ዘጋቢ፦ ተስፋየ ጋሹ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየትምህርት ቤት ደጅ የናፈቃቸውን ተማሪዎች በጋራ በመሥራት ወደ ዕውቀት መመለስ ይገባል።
Next articleለወባ ትንኝ መራቢያ የኾኑ ቦታዎችን በማጽዳት የወባ በሽታን መከላከል ይገባል።