የትምህርት ቤት ደጅ የናፈቃቸውን ተማሪዎች በጋራ በመሥራት ወደ ዕውቀት መመለስ ይገባል።

14

አዲስ አበባ: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 የሦሥት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በአማራ ክልል በትምህርት ዘርፉ ካጋጠሙ ፈተናዎች መካከል አሁን የተከሰተው የጸጥታ ችግር ዋነኛው ነው ብለዋል።

ሕጻናት ብዕር እና ወረቀት ይዘው በሚቦሩቁበት በዚህ ወቅት የትምህርት ቤት ደጅ የናፈቃቸው ተማሪዎች በርካታ ናቸው ብለዋል።

ይህን የትምህርት ክፍተት ለመሙላት የትምህርት ዘርፍ ተሳታፊ አካላትን ማስተባበር እና ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን ማምጣት ይገባል ነው ያሉት።

ያለፉት ሦሥት ወራት በተማሪ ምዝገባ እና በትምህርት ንቅናቄ አሳልፈናል ያሉት ኀላፊዋ ኾኖም የሚፈለገው የተማሪ ቁጥር ወደ ትምህርት ቤት ካለመምጣቱ በተጨማሪ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች በሰላም ችግር ምክንያት መጎዳታቸውን አንስተዋል።

በመድረኩ የሰሜን ሽዋ እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያዎች የሦሥት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለማሳያነት ቀርበዋል።

የሰሜን ሽዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዋሲሁን ብርሃኑ በዞኑ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ዘርፉ የነበረው ፈተና ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ይልቅ በቤታቸው እንዲውሉ አስገድዷል ብለዋል።

ለአብነት በ2017 ዓ.ም በዞኑ መመዝገብ ከነበረባቸው 570 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 263ሺህ ተማሪዎች ብቻ በትምህርት ገበታቸው ላይ ማሳለፋቸውን እና ቀሪዎቹ 307ሺህ ያህሉ ግን ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመለሳቸውን አስረድቸዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ለ2018 የትምህርት ዘመን ምዝገባ በፊደል ገበታው አባት ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ ስም “የተስፋ ቃል ኪዳን” በሚል ለወላጆች፣ ለተማሪዎች እና ለመምህራን ትውውቅ መደረጉንም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በሰላም ችግር ምክንያት ለሥነ ልቦና ችግር ለተዳረጉ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የትምህርት ማኅበረሰቡ ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል ምክትል ኀላፊው።

በዚህም ባለፉት ሦሥት ወራት 592ሺህ ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን 344ሺህ ተማሪዎች ብቻ ተመዝግበዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ በትምህርት ዘርፍ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በተለይም ከመምህራን እና የትምህርት ኀላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይት ወደ 94 ነጥብ 4 በመቶው መምህራን በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ተደርጓል ነው ያሉት።

የባለፉት የሦሥት ወራት ዋነኛ ሥራ የንቅናቄ መድረክ ማካሄድ ቢኾንም አሁንም ድረስ 822 ትምህርት ቤቶች ሥራ አልጀመሩም ነው ያሉት።

በተመሳሳይ መመዝገብ ከነበረባቸው 790 ሺህ ተማሪዎች መካከል 131ሺህ ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸውን እና ቀሪ ከ659 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመመለሳቸውን አንስተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው አሁን ላይ 79 በመቶ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን እና 51 በመቶ የሚኾኑ ተማሪዎች ደግሞ መመዝገባቸው ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ አደራው ምንውዬለት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጎንደር ከተማን የዲጅታል አድራሻ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ተፈረመ።
Next articleየጎንደር ከተማ ምክር ቤት አባላት በከተማዋ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ተመለከቱ።