
ጎንደር፡ ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማን ለማዘመንና አገልግሎት አሰጣጣጥን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የዲጅታል አድራሻ ሥርዓት ለመተግበር ሰነድ ተፈርሟል። ሰነዱ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና በስፔስ ሳይንስና ጅኦስፓሻል ኢንስቲትዩት መካከል ነው የተፈረመው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ዓለም እየዘመነ በመኾኑ ከጊዜው ጋር አብሮ መዘመን አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ጎንደር ከተማ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያላት መኾኑን ተከትሎ
የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ተግባራዊ መኾን አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በተለይ ጎንደር ከተማ ያሏትን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላ መኾኑን አስረድተዋል።
ጎንደር ከሰባት በላይ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሏት ከተማ በመኾኗ ወደ ከተማዋ የሚመጡ ጎብኝዎች ቆይታቸው ብሎም እንቅስቃሴያቸው ምቹ እንዲኾን የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።
የማዘመን ሥራው የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን ከፍ ያለ አበርክቶ እንዳለውም አንስተዋል። ይህም ምቹ ፣ ዘመናዊ ከተማ እና ንቁ ማኅበረሰብ በመፍጠር የዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ የሚያስችል መኾኑን አስታውቀዋል።
አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የዲጂታል ውጤት ሚናው ከፍተኛ መኾኑም ተነስቷል። ከተማ አሥተዳደሩ ለውጤታማነቱ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የስፔስ ሳይንስ እና ጅኦስፓሻል ኢንስቲቱዩት ምክትል ዋና ዳሬክተር በላቸው ፀሐይ ኢንስቲትዩቱ ልዩ ልዩ ተግባራትን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከእነዚህም ውስጥ በዲጅታል አድራሻ ሥርዓት ከተሞችን ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማስቻል አንዱ መኾኑን ጠቅሰዋል ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በ10 ዓመታት ውስጥ 73 ከተሞችን የሥርዓቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ እውቅና ያላት ጎንደር ከተማ የዲጅታል አድራሻ ሥርዓት ተጠቃሚ መኾኗ በቱሪዝም ዘርፉ ተመራጭ እንደሚያደርጋት አንስተዋል። ሥርዓቱ አዳማ፣ ጂማ እና ሀረር ከተሞችን ጨምሮ ሌሎች ከተሞች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የዲጅታል አድራሻ ሥርዓት ለፀጥታ አካላት፣ ለወንጀል መከላከል ተግባራት፣ ለቱሪዝም፣ ለፈጣን የጤና ወይንም የአምቡላንስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ፣ ለትራንስፖርት እና ሌሎችም ተቋማት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል። ለዚህም ተግባራዊነት እና ውጤታማነት ሁሉንም ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የመሬት ካዳስተር፣ የሊዝ አሠራርን ለማዘመን እና ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት መኾኑ ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!