በሰሜን ሸዋ ዞን ጉዳት እያደረሰ ላለው የትራፊክ አደጋ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።

3

ደብረብርሃን: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ቁጥጥር ዋና ክፍል የመንገድ ትራፊክ የግንዛቤ ማስጨበጫ ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ግሩም ዳኛቸው በ2018 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 33 የትራፊክ አደጋዎች መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በደረሱት አደጋዎች 24 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የገለጹት ኮማንደሩ 34 ሰዎች ከባድ፣ 26 ሰዎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ኀላፊው በዞኑ የትራፊክ አደጋ በአስከፊ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ አደጋው ከ2017 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በሞት 200 በመቶ፣ በከባድ የአካል ጉዳት 325 በመቶ እንዲሁም በቀላል የአካል ጉዳት 271 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።

በንብረት የደረሰ ጉዳት እና ውድመትም ከፍተኛ መኾኑን የገለጹት ኮማንደር ግሩም ስድሰት ተሽከርካሪዎች ከባድ የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ሲኾን 16 ተሽከርካሪዎች ደግሞ ቀላል የንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

የደረሰው የንብረት ውድመት በገንዘብ ሲሰላ 14 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር እንደሚገመትም ነው የተናገሩት።

ከደረሱት አደጋዎች 84 በመቶው በአሸካርካሪው ጥፋት የተፈጠሩ ስለመኾናቸውም ገልጸዋል። ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ ቀኝን ለቆ ማሽከርከር፣ በጠመዝማዛ መንገድ ላይ ለመቅደም መሞከር ለአብነት ከሚጠቀሱ እና አደጋን ካስከተሉ የአሸካርካሪዎች ስህተቶች እና የሥነ ምግባር ችግሮች ውስጥ መኾናቸውን አብራርተዋል።

እንደ ተቋም የተለያዩ ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የትራፊክ ፍሰትን ሰላማዊ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ አስገንዝበዋል። ይሁን እንጂ የትራፊክ አደጋ አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ተበራክቷል ነው ያሉት።

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በቅንጅት እና በኀላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

አሽከርካሪዎች ሙያዊ ሥነ ምግባርን እና ሕጎችን አክብረው እንዲያሽከረክሩ፣ ባለንብረቶችም የተሸከርካሪዎችን የቴክኒክ ደኅንነት በተገቢው እንዲያረጋግጡ፣ ተሳፋሪዎች እና እግረኞችም የሚጠበቅባቸው ኀላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል።

የትራፊክ አደጋ በሰው ሕይወት፣ በአካል እና በንብረት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በመረዳት የአሸካርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት የትራፊክ አይጋን በጋራ ለመከላከል በቁጭት ሊሠሩ ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሥነጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአጀንዳ ማሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በንቃት ተሳትፈዋል።
Next articleጎንደር ከተማን የዲጅታል አድራሻ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ተፈረመ።