በአጀንዳ ማሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በንቃት ተሳትፈዋል።

3

አዲስ አበባ: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኮሚሽኑ ከዲያስፖራው አጀንዳ የማሠባሠብ እና ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራ በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በስዊዲን እና በእንግሊዝ መካሄዱን ጠቅሰዋል።

በእነዚህ መድረኮች በአካል መገኘት ያልቻሉ ተሳታፊዎችም በበይነ መረብ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ውይይት በተካሄደባቸው መድረኮች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ቅድመ ውይይቶች መካሄዳቸውንም ጠቅሰዋል።

ወደ አጀንዳ አሠባሠቡ ከመገባቱ በፊትም ተሳታፊዎቹ ስለ ምክክር መሠረታዊ ጉዳዮች፣ ኮሚሽኑ ስላከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት፣ ሂደቱን በገለልተኝነት እና በነጻነት ለማካሄድ ያለውን አሠራር በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡

ተሳታፊዎች እንደ ሀገር ለገጠሙ ያለመግባባት እና የሃሳብ ልዩነቶች መንስኤ ናቸው ያሏቸውን አጀንዳዎች ተመካክረው በመለየት ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡

የተለያዩ የማኅበረሰብ አደረጃጀት ተወካዮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎችም አካላት በመድረኩ እንደተሳተፉ ተጠቁሟል።

የምክክር መድረኮቹ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መብታቸውን ተጠቅመው በንቃት የተሳተፉባቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል አጀንዳ ለማሠባሠብ እና ተወካዮችን ለማስመረጥ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በሁለት ዙር በተደረጉ ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን መሠረት በማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ከሕዝባዊ መድረኮች የተሠባሠቡ አጀንዳዎችን የማደራጀት እና የማጠናቀር፣ ለምክክር ጉባኤው አስፈላጊ የኾኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ለማጠናቀቅ ጥረቶች እየተደረጉም ነው ብለዋል።

በቀጣይም የአጀንዳ ቀረጻ እና የምክክር ጉባኤ የሚካሄድባቸውን የአሠራር ሥርዓቶች እና ዝርዝር የማስፈጸሚያ ዕቅዶችን የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሰሜን ሸዋ ዞን ጉዳት እያደረሰ ላለው የትራፊክ አደጋ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።
Next articleበሰሜን ሸዋ ዞን ጉዳት እያደረሰ ላለው የትራፊክ አደጋ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።