
ደብረማርቆስ: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የገበያ ማረጋጋት እና የሕገ ወጥ የንግድ ቁጥጥር ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ እንዲከናወኑ ለማድረግ ግብረ ኀይል ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮሴፍ መለሰ አሁን ላይ በገበያው ላይ የምግብ እና የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ መኾኑን ገልጸዋል።
ምርትን ያለ አግባብ በሚያከማቹ አንዳንድ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ ክትትል እና ርምጃ እየተወሰደ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በንጉሥ ተክለሃይማኖት ክፍለ ከተማ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ በነበረ ነጋዴ ላይ አስተማሪ እርምት መወሰዱንም ለአብነት አንስተዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በአራቱም ክፍለ ከተሞች የገበያ ማረጋጋት፣ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር የግብይት ሂደቱ የተረጋጋ እና ጤናማ እንዲኾን ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪን ተከትሎ ሊከሰት የሚችል ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር አደረጃጀቶች መፈጠራቸውንም አብራርተዋል። አደረጃጀቶቹም ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም የክትትል፣ የቁጥጥር እና እርምት የመውሰድ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
ሸማቾች በተረጋጋ መልኩ ግብይት በመፈፀም እና ነጋዴዎችም ሕጋዊ መስመርን ተከትለው በመንቀሳቀስ ሕገወጥነትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን