በአንድ ሀገር ውስጥ ጤናማ የትውልድ ቅብብሎሽ ሊኖር የሚችለው ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ሥርዓት ሲፈጠር ነው።

6
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር መልካሙ ባየ የአምስት ልጆች አባት ናቸው። ትምህርት ለሰው ልጆች ያለውን ጠቀሜታ ቢረዱም እንኳን ሙሉ በሙሉ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ አልላኩም።
አርሶ አደር መልካሙ ባየ አሁን ላይ ቤት ውስጥ ያሉትን ልጆች ግን ወደ ትምህርት እየላኩ እንደኾነ ገልጸዋል። ግጭት እና ሰላም ማጣት ልጆች በትምህርታቸው ካሰቡበት ሳይደርሱ በእንጭጩ ማስቀረቱን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ልጆቻቸው ተምረው ግብርናውን ያዘምናሉ፣ ተምረው ሀገርን ወገንን ይጠቅማሉ በሚል አስበው ማስተማር ቢጀምሩም የተፈጠረው ችግር የልጆቹን የሕይዎት መሥመር መቀየሩን ነው የተናገሩት።
በፎገራ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአንዱ ትምህርት ቤት መምህር የኾኑት መሠረት ስጦታው በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት አሁን ላይ በአግባቡ ሁሉም መምህራን መገኝታቸውን ነግረውናል።
ትምህርት ቤቱ ግን ተማሪወቹን ለማስተማር የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልኾነ ነው የተናገሩት።
ትምህርት ቤቶቹ ፈራርሰው፣ የሚያስተምሩባቸው ሰሌዳዎች ተቀዳደው፣ መጸሐፍቶች ወድመው እንዳገኟቸውም ነው ያብራሩት። ይሁን እንጅ ባለውም ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
መምህርቷ ትምህርት ሁልጊዜ በኅብረተሰብ ውስጥ ከፍ ያለ ለውጥ ለማምጣት ሁነኛ መሳሪያ መኾኑን አስረድተዋል።
በመኾኑም መንግሥት የትምህርት ቁሳቁስን እና ትምህርት ቤቱን በማስተካከል ልጆች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ እንዲሠራም ጠይቀዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው በፎገራ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት በርእሰ መምህርነት የሚያገለግሉት አራጋው ሀብታሙ እንደገለጹት ትምህርት ቤት ላይ መምህራን ተሟልተው ተገኝተዋል።
ርእሰ መምህር አራጋው ሀብታሙ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ በአግባቡ እየላኩ ባለመኾኑ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲልኩ አሳስበዋል።
ከአንደኛ ክፍል እስከ አራተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በአግባቡ ወደ ትምህርት ቤቶች እየመጡ እንደኾነም ተናግረዋል።
ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ግን ቤተሰቦቻቸው አርሶ አደር በመኾናቸው ለጉልበት ሥራ ሲሉ እያስቀሯቸው እንደኾነም ጠቁመዋል።
ትምህርት የተሻለ ዕውቀት ለማግኘት እና በጎ ተፅዕኖ ለማምጣት አቅም ይኾናል ያሉት ርእሰ መምህሩ ይህ ጉዳይ ችላ ሊባል እንደማይገባ ነው ያሳሰቡት።
ዛሬ ላይ በአግባቡ የተማሩ ልጆች ነገ ለቤተቦቻቸው የሚደርሱ መኾናቸውን ወላጆች ሊገነዘቡት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። ትምህርት የበለጸገ ሕይዎት ለመምራት ተመራጭ መንገድ ነውም ብለዋል።
የፎገራ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይበልጣል ጓዴ በትምህርት ዙሪያ እንደ ወረዳ በሁሉም መስኮች ኮሚቴዎችን በማዋቀር በሁሉም ትምህርት ቤት ትምህርት እንዲጀመር ተደርጓል ብለዋል።
ወደ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ያላኩ ወላጆችም ግንዛቤያቸውን የመጨመር ሥራ በየደረጃው እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
ወላጆች ልጆቻቸው በጸጥታ ምክንያት በትምህርታቸው ሲጎዱ የቆዩ ልጆችን አሁን ደግሞ በሥራ ምክንያት መጉዳት እንደሌለባቸው ተናግረዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ወሳኝ መኾኑን ነው ያብራሩት።
ትምህርት ለነገ የማይባል ጉዳይ በመኾኑ የባከነውን የትምህርት ዓመት ለማካካስ ተማሪወች፣ መምህራን፣ ወላጆች እና ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያዱርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleኅብረተሰቡ የፍትሕ አገልግሎትን እንዲያገኝ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
Next articleስለ ጋንግሪን በሽታ ምን ያህል ያውቃሉ ?