
ፍኖተ ሰላም: ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ ከወረዳ እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ አካሂዷል።
ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ተግባርን በማከናወን ኅብረተሰቡ የፍትሕ አገልግሎት እንዲያገኝ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩም ይገኛሉ።
ባለፈው በጀት ዓመት የነበረው የጸጥታ ችግር በምዕራብ ጎጃም ዞን የዳኝነት እና መደበኛ የፍርድ ቤት ተግባራት በሚፈለገው ልክ ለማከናወን እንቅፋት መፍጠሩን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዓባይነህ ካሴ ተናግረዋል።
ተገልጋዮች በጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት ባለመምጣታቸው የተሟላ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት አለመቻሉንም አንስተዋል።
ይሁን እንጅ አስቻይ ሁኔታ ባለባቸው አካባቢዎች የመጡ ጉዳዮች ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ 93 በመቶ እንዲሁም የወረዳ ፍርድ ቤቶች ደግሞ 89 በመቶ በመፈፀም ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።
በተያዘው በጀት ዓመት የዳኝነት አገልግሎት እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የላቀ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እና ቅንጅታዊ አሠራሮችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለኅብረተሰቡ ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ፕሬዝዳንቱ ዓባይነህ ጠቁመዋል።
በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሥራ ያልገቡ ፍርድ ቤቶችን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ በማስገባት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራም ነው ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ የቡሬ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት መንገሻ በላይ ከዚህ በፊት እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ መዝገቦች መፍትሔ ያገኙ የነበረ ቢኾንም በጸጥታ ችግሩ ምክንያ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት ባለመምጣታቸው 2 ሺህ 500 መዝገቦች ብቻ እልባት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ የጃቢጠህናን ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አበበ ሽታየ በቀጣይ በጀት ዓመት ተዘዋዋሪ ችሎቶችን በማስፋት የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
ለዲጂታላይዜሽንም ትኩረት በመስጠት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ በማድረግ የኅብረተሰቡን እርካታ ለመጨመር እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን