
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር (ኢንሳ) ጋር በመተባበር 6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወርን አስመልክቶ በባሕር ዳር ከተማ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው የቆየውን አሠራር ተላምዶ የመቀመጥ እና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ፈቃደኛ ያለመኾን ውስንነት እንዳለ ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ አሠራር አለመኖር እና ቴክኖሎጂን የሚተገብር ባለሙያ ማነስ ዲጂታላይዜሽንን ለመተግበር ፈተና ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።
በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ያላቸውን ተቋማት በመምረጥ የቴክኖሎጂ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ለቴክኖሎጂ ዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደሰጠም ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ማስፋት እና ሲሰተሙን መጠቀም ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ምክትል ኀላፊው የሲሰተሙም ኾነ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቱ ደኅንነት መጠበቅ ካልቻለ ሁሉ ነገር ዋጋ ቢስ ይኾናል ነው ያሉት። የሲስተሞችን ደኅንነት መጠበቅ አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሳይበር ደኅንነት ኦዲትን ያላለፈ ማንኛውም ሲስተም ወደ ሥራ እንደማይገባም ገልጸዋል። የሳይበር ደኅንነትን ጉዳይ አውቆ የሚጠቀም ተጠቃሚ እንዲኖር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
የሳይበር ደኅንነት ወርን ማክበር የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤ እንዲያድግ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ሁሉም ሰው መረጃ አለው፤ ሁሉም ሰው መረጃውን መጠበቅ አለበት ነው ያሉት። ለሳይበር ደኅንነት ትኩረት እንደሚደረግም አመላክተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬከተር ዮዳሔ አርዓያሥላሴ ቴክኖሎጂው እያደገ በፍጥነት እየተራመደ መኾኑን ገልጸዋል።
ዲጂታላይዜሽንን ማሳደግ የተመረጠው ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሳይበር ደኅንነቱ ካልተጠበቀ ባንጠቀመው ይሻል ነበር የሚል ጉዳት እንደሚያደርስ ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ጎን ለጎን ግን የሳይበር ደኅንነት ላይም ግንዛቤን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት። የሳይበር ደኅንነት አሥተዳደርን ማስተካከል እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
አሁን ላይ በየትኛውም የሥራ መስክ ያለ ሁሉ ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ የሚለው ጊዜ ነው ብለዋል። የሀገርን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሳይበር ደኅንነት ላይ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ዲጂታላይዜሽንን ለመጠቀም ሙያውን በተገቢው የሚረዳ መሪ እና ባለሙያ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ዲጂታላይዜሽን በአግባቡ ለመጠቀም የቴክኖሎጂ ብቃትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ከተሞችን ዘመናዊ ለማድረግ የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። ዲጂታላይዜሽንን መሠረት አድርገን የምንሰጣቸው አገልግሎቶችም አዳጊ እንዲኾኑ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ባሕር ዳር ከተማን ለማዘመን እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። መረጃዎችን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ከተማዋን በደኅንነት ካሜራዎች የመጠበቅ ሥራ እየተሠራ እንደኾንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ሲሺል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረ ማርያም ዲጂታላይዜሽን ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። ዲጂታላይዜሽንን በአግባቡ ለመጠቀም የግንዛቤ ፈጠራ ላይ ቀድሞ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የዲጂታላይዜሽን አጠቃቀማችን ጠንካራ እና የሳይበር ደኅንነታቸው ካልተጠበቀ በምንሰጠው አገልግሎት ሕዝቡ እምነት አይኖረውም ነው ያሉት። በሚሰጡ አገልግሎቶች ሕዝቡ አመኔታ እንዲኖረው የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በዲጂታላይዜሽን ላይ ከሚፈለገው ደረጃ ለመድረስ የሰው ሃብት ልማት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። የሰው ሃብት ልማትን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች የማሠልጠኛ ተቋማት ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
የመንግሥት አገልግሎት አሥተዳደርን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ሕዝብን እያማረሩ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አንስተዋል።
ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት የአገልግሎት አሠጣጥን ዘመናዊ ማድረግ እና የዜጎችን እንግልት ማስቀረት ይገባል ነው ያሉት። በቴክኖሎጂ አማካኝነት የሕዝብን ችግር መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!