በጎነት ባሕል ኾኖ መቀጠል ይገባዋል።

3
ደብረ ታቦር: ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ ማጠቃለያ እና የ2018 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የክረምት በጎ ፈቃደኞች በጎነት ባሕል ኾኖ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተማሪዎች ቁሳቁስ በማሟላት፣ ቤት በማደስ፣ መንገድ በመጠገን፣ አልባሳት በመሠብሠብ እና በሌሎችም የበጎ ተግባራት ሥራ ውጤታማ መኾን ተችሏል ነው ያሉት።
ለቀጣይ በክረምት ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ስሜነህ ደሳለኝ የሁሉም ማኅበረሰብ ተሳትፎ መኖር የክረምት በጎ ተግባር የተሳከ እንዲኾን አስችሏል ነው ያሉት።
በክረምት በጎ ፈቃድ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት አቶ ስሜነህ ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ፣ የማዕድ ማጋራት፣ አዲስ ቤት የመሥራት እና የመጠገን እንዲሁም የትህምርት ቁሳቁስ ድጋፍ ዋናዋናዎቹ የበጎ ተግባር ሥራዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።
አቶ ስሜነህ እንዳሉት በዞኑ የነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ውጤታማ ነበር፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በጎነት ክረምት እና በጋ ተብሎ ጊዜ የሚወስነው ተግባር ሳይኾን ሁሌም የተቸገረን መርዳት ነው ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው ናቸው። በክረምት ወቅት የነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴም የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ለቀጣይም ሰው ተኮር ተግባራት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል። በተለይ የትምህርት እንቅስቃሴ እና ወጣቱ አላስፈላጊ ቦታ ላይ እንዳይውል ከማድረግ አኳያ መሥራትም ይገባል ነው ያሉት።
በጎነት ለራስ ነው ያሉት አቶ መንበር በዞኑ የተሠሩ ተግባራት ከሌላው ጊዜ በተለየ የተሻለ ትምህርት የተወሰደባቸው እና ውጤታማም ናቸው ብለዋል። ለበጎ ተግባሩም ሁሉም አካላት ርብርብ ያደረገበት መኾኑንም ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ለ90 ቀናት ብቻ የሚከናወን ተግባር ሳይኾን ሁሌም አብሮ መዝለቅ እንዳለበት አሳስበዋል። በመልካም ተግባር እንቅስቃሴዎች የተሳተፉ አካላትንም አመሥግነዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አስራቴ በበጎ ፈቃድ ተግባር የተሠራው ሥራ የመንግሥትን ወጭ የቀነስ ትልቅ ተግባር ነው ብለዋል።
በእያንዳንዱ ወረዳ በመናበብ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በማንሳት ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
የበጋ በጎ ፈቃድን ተግባራዊ ለማድረግ የተደራጀ ዕቅድ ማቀድ እና አደረጃጀቱን የተቀናጀ ማድረግም ይገባል ነው ያሉት።
ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን ማጠናቀቅ፣ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እና በሰላም እና ጸጥታ ላይ ትኩረት አደርጎ መሥራት የቀጣይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ትኩረቶች ናቸው ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleከ280 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተከናውነዋል።
Next article“90 በመቶ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በግንዛቤ ክፍተት ይከሰታል” የሳይበር ደኅንነት ባለሙያ