
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር ከዩኒሴፍ እና ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ”ብቁ ወጣት” የተሰኘ መርሐ ግብር የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል።
በዩኒሴፍ የአማራ ክልል ጽሕፈት ቤት ተወካይ አሥተባባሪ ዶክተር አምባነሽ ነጮ የብቁ ወጣት መርሐ ግብር ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን የወደፊት ዕድል ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንደኾነም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ በግጭት የተጎዱት የአማራ፣ የትግራይ እና አፋር ክልሎች ላይ የሚተገበር ቢኾንም 59 በመቶ ድርሻ የሚይዘው አማራ ክልል ነው ብለዋል፡፡ ለሦሥት ዓመታት በክልሉ በ23 ወረዳዎች ይተገበራልም ነው ያሉት፡፡
መርሐ ግብሩን የሚያስፈጽመው በክልሉ የሕዝብን ተሳትፎ በማሳደግ የሚታወቀው አማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) ነው ብለዋል። ከዚህ መርሐ ግብር ሦሥት መሠረታዊ ውጤቶች ይጠበቃሉ ነው ያሉት።
እነዚህም ወጣቶችን በሳይኮ ሶሻል ድጋፍ ለሥራ ዝግጁ ማድረግ፣ በትምህርት በሥራ እና በክህሎት ዘርፍ መደገፍ እና ከትምህርት የወጡ ወጣቶችን አለያም ትምህርት ላይ ኾነው ወደ ሥራ ማሸጋገር ናቸው ብለዋል።
ይህ መርሐ ግብር ልዩ የሚያደርገው ተግባሩን ወደ ወጣቱ ለማድረስ በርካታ ተቋማት የሚሳተፉበት በመኾኑ እንደኾነ ጠቁመዋል። ይህም የተለያዩ ሴክተሮችን አቅም ያሳድጋል ነው ያሉት።
መርሐ ግብሩ የወጣቶችን ሕይወት የሚቀይር እና ማኅበረሰባቸውን ለማሳደግ ሞዴል እንዲኾኑ የሚያግዝ በመኾኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል በጋራ እንዲሠራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መላኩ ፈንታ የልማት ማኅበሩ የራስን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት የሚንቀሳቀስ ተቋም እንደኾነ ገልጸዋል።
”በትምህርት የተቀየረ እና ጤንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብ ለሀገር ልማት ግንባታ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው”ም ብለዋል። ለዚህም ማኅበሩ በትምህርት እና ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በትብብር የማኅበረሰብ ችግርን ለመፍታት ከማኀበረሰቡ፣ ከመንግሥት፣ እና ከረጅ ተቋማት ጋር እንደሚሠሩም አንስተዋል።
የብቁ ወጣት መርሐ ግብር ከረጅ ድርጅቶች ጋር ከሚሠሩ ተግባራት መካከል አንዱ ነውም ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በሙሉ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ለመተግበር ዝግጅት እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡
በክልል ደረጃ እስከ ወረዳ ከ13 ተቋማት ጋር በትብብር እና በተደራጀ መንገድ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት በሦሥት ዓመቱ 67ሺህ በአንድ ዓመት ደግሞ 23ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
የሚከናወኑ ተግባራትም የአዕምሮ ጤና ድጋፍ፣ ወደ ትምህርት የሚመለሱትን መመለስ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንደኾኑም ጠቁመዋል።
ይህ ትልቅ ፕሮጀክት ከተሳካ ለወጣቶች እና ለማኅበረሰቡ ትርጉም ያለው ለውጥ እና ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ስለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የወጣቶችን ጉዳይ በእኔነት ስሜት በመተባበር እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አሥተባባሪ፣ የትምህርት ቢሮ ኀላፊ እና የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር ቦርድ ሠብሣቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ፕሮጀክቱ ባለው አቅም ውስንነት በተመረጡ ወረዳዎች ይተገበራል ነው ያሉት፡፡
አንዳንዱ በተደጋጋሚ ተጠቃሚ እንዳይኾን ሌላው ደግሞ እንዳይረሳ በጥንቃቄ መሠራት አለበትም ብለዋል፡፡
ለዚህ ሥራ የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በቁርጠኝነት እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ በመተባበር ለፕሮጀክቱ መሳካት እንዲሠሩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!