የቅድመ ወባ መከላከል ክትባት እየተሰጠ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ። 

4

ገንዳ ውኃ፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ዕድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 11 ወር ለኾኑ ሕጻናት የቅድመ ወባ መከላከል ክትባት በመደበኝነት እየተሰጠ መኾኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል።

 

የቅድመ መከላከል ክትባቱ በገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጣቢያ ነው እየተሰጠ የሚገኘው።

 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ አካባቢው ሞቃታማ በመኾኑ የወባ ወረርሽኝ በሽታ በብዛት ይከሰታል ብለዋል። ማኅበረሰቡ ለበሽታው ተጋላጭ እየኾነ መምጣቱንም ተናግረዋል። የወባን በሽታ ለመከላከል የቅድመ ወባ መከላከል ክትባት ዛሬ መሰጠት መጀመሩንም ምክትል ኀላፊው ተናግረዋል።

 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዮሴፍ ጉርባ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት በአንድ ከተማ አሥተዳደር እና በአንድ የወረዳ ከተማ የቅድመ ወባ መከላከል ክትባት በመደበኛነት እንዲሰጥ ማስጀመራቸውን ተናግረዋል።

 

ክትባቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በጋራ በመሥራት በወባ ተጠቂ ለኾኑ አካባቢዎች እንዲሰጥ መደረጉንም ገልጸዋል።

 

ክትባቱ ከ6 ወር እስከ 11 ወር ባሉ የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሕጻናት በመደበኛነት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

 

ወላጆች ልጆቻቸውን በክትትል እና በአግባቡ ማስከተብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 

በዞኑ የወባ በሽታን ለመከላከል የታቆረ ውኃን የማፋሰስ እና ኬሚካል የመርጨት፣ የማዳፈን፣ ቆሻሻን የማቃጠል እና ሳርን የማጨድ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል።

 

የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲስተር ምግብ ፈንታ ለወባ በሽታ በአብዛኛው ተጋላጭ የሚኾኑት ሕጻናት መኾናቸውን ተናግረዋል።

 

ሕጻናት ደግሞ በሽታን የመከላከል እና የመቋቋም አቅም ስለሌላቸው በሽታው በቶሎ ያጠቃቸዋል ነው ያሉት። ሕጻናት በወባ በሽታ እንዳይጠቁ የቅድመ መከላከል ክትባት እየተሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል።

 

ክትባቱን መከተብ የጀመረ ሕጻን ለአራት ዙር መከተብ እዳለበት እና ክትባቱ በተከታታይ በ6ኛ፣ በ7ኛ፣ በ9ኛ እና በ15ኛ ወር ላይ እንደሚሰጥም አብራርተዋል።

 

ክትባቱን የሚሰጥ ባለሙያ ከዚህ በፊት የክትባት ባለሙያ የኾነ እና አሁን ደግሞ ለሚሰጠው ክትባት ተገቢውን ሥልጠና የወሰደ መኾኑን አስገንዝበዋል።

 

የተሰጠው ክትባት የማቅለሽለሽ፣ የማሞቅ እና የማስለቀስ ምልክት ስላለው እናቶች በሚያስተውሏቸው በእነዚህ ምልክቶች እንዳይደናገጡ አሳስበዋል።

 

ከተገለጸው ምልክት ውጭም የኾነ ነገር ካለ ወደ ጤና ተቋማት መምጣት እንዳለባቸው ሲስተር ምግብ አሳስበዋል።

 

ወላጆችም ሕጻናትን በአግባቡ ማስከተባቸው ልጆች ጤናማ እና ብርቱ ሁነው እንዲያድጉ ይረዳቸዋል ነው ያሉት።

 

ልጆች ከተለያዩ ወረርሽኝ በሽታ እንዲጠበቁ የቅድመ ወባ መከላከል ክትባት እንዲወስዱ በመደረጉ ደስተኛ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

 

ቀጣይም ወባን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አካባቢን የማጽዳት እና የማስዋብ ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕል ፍርድ ቤቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ውይይት ተደረገ።
Next articleየክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የድርሻን መወጣት ይገባል።