
ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል። የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢነት የሚመራ የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞለታል።
በዛሬው ዕለትም አማካሪ ምክር ቤቱ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሥራ እንዲጀምሩ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
እስከ አኹን ድረስ አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የሕግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አብራርተዋል። የትግበራ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
በባሕል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ የሚደረጉትን እና በየአካባቢው ያሉ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ እና የሽምግልና ሥርዓቶችን በጥናት የመለየት ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።
በውይይቱ ለባሕል ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ የሽምግልና ሥርዓቶች እውቅና መስጠት፣ በየቀበሌው ማቋቋም እና ማደራጀት፣ የማስቻያ ቦታዎች ማዘጋጀት፣ ሀብት የማሰባሰብ ተግባራት፣ ሥልጠናዎችን መሥጠት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ተነስተዋል።
በየደረጃው ካሉት የመንግሥት አስፈጻሚዎች እና ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው በውይይቱ የተገለጸው። የአማካሪ ኮሚቴው አባል ተቋማት ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተመላክቷል።
በአዋጁ የተቀመጠውን ዓላማ ለማሳካት የአማካሪ ምክር ቤቱ አባል ተቋማት የተጣለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚኖርባቸው አቶ ዓለምአንተ አስገንዝበዋል።
አማካሪ ምክር ቤቱ በቀጣይ እየተገናኘ የሚመክርበትን እና የሚሠራበትን አቅጣጫ አስቀምጧል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!