
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ኤርትራ እስከተገነጠለችበት 1983 ዓ.ም ድረስ 97 በመቶ የሚኾነው የወጭ እና ገቢ ንግዷን ታከናውን የነበረው በአሰብ በኩል እንደነበር የትናንት ታሪክ ምስክር ነው፡፡
ከኤርትራ መገንጠል በኋላ ደግሞ የባሕር በር አልባ የኾነችው ኢትዮጵያ አሰብን በኪራይ ስትጠቀም መቆየቷም የትናንት ትውስታ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በ1990 ዓ.ም መቀስቀሱን ተከትሎ የአሰብ ወደብ ተዘጋ፡፡ በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡
በወቅቱ ኢትዮጵያ የነበራት አማራጭ የጂቡቲ ወደብን መጠቀም ነበር፡፡ የጂቡቲ ወደብ በወቅቱ የኢትዮጵያን አንድ አራተኛ ብቻ የሚኾነውን የወደብ ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል አቅም የነበረው በመኾኑ፣ በኢትዮጵያ ትልቅ የሎጂስቲክስ ብሎም የብሔራዊ ደኅንነት ችግር እንዲያጋጥም ኾኗል፡፡
ከ1993 ዓ.ም በኋላ ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የጂቡቲ ወደብ ማስፋፊያ ተደረገለት፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከ90 እስከ 97 በመቶ የሚኾነውን ንግድ ለማከናወን የጂቡቲን ወደብ በመፍትሔነት እየተጠቀመች ነው።
በተለይ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር እና በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ላላቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች የባሕር በር የደም ስር ያህል አስፈላጊ ነው። የባሕር በር ተደራሽነት እና የኢኮኖሚ ዕድገት እጅግ የተሳሰሩ ጉዳዮችም ናቸው፡፡
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህሩ አንዱዓለም በጋሻው እንዳሉት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በቀጣናው ካየለው የጦር ፍክክር ባለፈ ለኢኮኖሚ እድገቷ ያስፈልጋታል ነው ያሉት። የባሕር በር ለኢትዮጵያ በጣም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ሀገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ በሙሉ የባሕር በር አያስፈልገንም ሊል አይችልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ልትገነባበት የምትችለውን ገንዘብ ለወደብ ኪራይ እየከፈለች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
ስለዚህ የባሕር በር ማግኘት ብንችል ከጅኦ ፖለቲካው ጉዳይ ውጭ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችን በጣም እየጨመረ ይመጣል ነው ያሉት። የባሕር በር ማግኘት መቻል የታሰበውን የእድገት ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን ነውም ብለዋል።
አሁን ከምንጠቀምበት የጅቡቲ ወደብ – አዲስ አበባ ወይም መሀል ሀገር እስኪደረስ የሚወስደው ጊዜ እና ገንዘብ ከፍተኛ ነውም ብለዋል። በቅርብ ርቀት የምትገኘው እና ከ60 እስከ 90 ኪሎ ሜትር የሚወስድ መንገድ ያላት አሰብን ግን መጠቀም አልቻልንም ነው ያሉት።
አሰብ ለኢትዮጵያ ባለፋት 30 ዓመታት በላይ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ብለዋል። ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ዳርቻ ታሪካዊ የይዞታ ባለቤት ናት፤ የአሰብም ባለርሰት ሀገር የኾነችው ኢትዮጵያ ዝግ የኾነች ሀገር (land lock) ልትሆን አይገባም ነው ያሉት።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከመጠን በላይ እየጨመረ ነው፤ ኢትዮጵያውያን የባሕር በር ሊቆለፍብን አይገባም ብለዋል።
የጊዜ ጉዳይ እንጅ መንግሥት ባያነሳው እንኳ በትውልዱ የሚነሳበት ጊዜ ሊኖር እንደሚችልም ተናግረዋል። የትውልዱ የባሕር በር ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝም በጥናት እና ምርምር መደገፍ አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!