ከነበረው ንቅናቄ በላይ ጥረት በማድረግ የወባ በሽታን መከላከል ይገባል። 

8

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ ወባ እንዳይስፋፋ ከወዲሁ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

 

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ወባ በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳያስከትል ከወዲሁ በትኩረት መሠራት ይገባል ብለዋል። በክልሉ ካሉ ወረዳዎች ውስጥ በተለይ 40ዎቹ የክልሉን 70 በመቶ የሚኾነውን የዋባ ስርጭት የሚሸፍኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።

 

በእነዚህ ወረዳዎች በተለይ ጥቅምት፣ ሕዳር እና ታኅሣሥ ወር ላይ ወባ በሰፊው ስለሚያጠቃ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።

 

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ከዚህ በፊት ከነበረው ንቅናቄ በላይ ጥረት በማድረግ የወባ በሽታን መከላከል ይገባል ብለዋል።

 

ወባ በክልሉ ችግር ነው ያሉት ኀላፊው አምራቹን ዜጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው መኾኑን ነው የተናገሩት። በዚህም ኅብረተሰቡን ባለቤት በማድረግ በተከታታይ ወባን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

 

የሚዲያ ተቋማት እና አጋር አካላትም በሁሉም ዘርፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የወባ ወረርሽኝ “የአርብ ጠንካራ እጆች ወባን ይገታሉ” በሚል መሪ መልዕክት ባለፈው ዓመት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ሴቶች፣ ሕጻናት እና አረጋውያንን ከበሽታው መከላከል ተችሏል ብለዋል።

 

ዘንድሮም ያለፈውን በማጠናከር እና የአልጋ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም ወባን መከላከል ይኖርብናል ነው ያሉት። ወረርሽኙን ለመከላከል ሁላችንም ከቤታችን መጀመር ይኖርብናል ብለዋል።

 

የወባ መራቢያ የሚኾኑ ቦታዎችን በማጽዳት እና በማፋሰስ ወባን የመከላከል ሥራ ማከናወን እንደሚገባ አመላክተዋል።

 

የአማራ ክልል ጤና ቢር ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ወባ በሽታ የክልሉን 80 በመቶ በላይ አካባቢዎች እያጠቃ ያለ አደገኛ በሽታ ነው ብለዋል።

 

በሽታው ከአምናው አንጻር ሲታይ የቀነሰ ቢኾንም አሁንም የኅብረተሰቡ የጤና ችግር ኾኖ ቀጥሏል ነው ያሉት።

 

ሁሉም ጤና ጣቢያዎች፣ ጤና ኬላዎች እና ጤና ተቋማት “የአርብ እጆች የወባ በሽታን ይገታሉ” የሚለውን ንቅናቄ በትኩረት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

 

ዘጋቢ: ሰናይት በየነ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በራይላ ኦዲንጋ ሕልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ። 
Next articleኢትዮጵያውያን የባሕር በር ሊቆለፍብን አይገባም።