የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፖሊስ ተቋምን መቀላቀላችሁ የሚያስመሰግናችሁ ተግባር ነው። 

3

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሸነር ታደሰ አያሌውን ጨምሮ የስትራቴጅክ እና ከፍተኛ መሪዎች የ34ኛ ዙር የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ምልምል ፖሊሶች የሥልጠና ሂደት ጎብኝተዋል።

 

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እና የክልሉን የጸጥታ ስጋት ለመቆጣጠር ልዩ ልዩ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል። ከተግባራቱ መካከል ምልምል ፖሊሶችን በማሠልጠን የፖሊስን አገልግሎት ለሕዝቡ ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው።

 

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የ34ኛ ዙር መደበኛ እና የአድማ መከላከል ሠልጣኝ ምልምል ፖሊሶችን በብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት እያሠለጠነ ይገኛል።

 

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ

ረዳት ኮሚሸነር ታደሰ አያሌው ፖሊስ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት በመራቅ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

 

ወንጀልን ቅድሚያ በመከላከል ላይ ያተኮረ አሠራርን በመከተል፣ ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ምርመራ በማጣራት አጥፊው በሕግ እንዲጠየቅ በማድረግ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ ከፖሊስ የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።

 

ክልሉ ችግር በገጠመው ጊዜ ግንባር ቀደም በመኾን የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፖሊስ ተቋምን መቀላቀላችሁ የሚያስመሰግናችሁ ተግባር ነው ብለዋል። ሥልጠናችሁን አጠናቃችሁ ስትመደቡ የክልሉን ሕግ የማስከበር አቅም ከፍ ታደርጋላችሁ ነው ያሉት።

 

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ ፖሊስነት በርካታ ውጣ ውረዶችን የሚያሳልፍ፣ ቁርጠኛ፣ ትግዕሰተኛ፣ በቅንነት ሕዝብን የሚያገለግል እና ሰብዓዊነትን የሚያስቀድም ሙያ ነው ብለዋል።

 

ፖሊስነት ለሰላም መከበር እስከ ሕይወት መስዕዋትነት መክፈልን የሚጠይቅ ሙያ መኾኑንም ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የሚሰጡ የመስክ እና የክፍል ትምህርቶች ይህን ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውን አንስተዋል።

 

ለነገ የሕዝብ እና የመንግሥት ተልዕኮዎች ራሳችሁን ዝግጁ በማድረግ ቀሪ የሥልጠና ጊዜያችሁን በውጤታማነት ማጠናቀቅ አለባችሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

 

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያው የሰው ሀብት አሥተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አብዮት ሽፈራው ሠልጣኝ ምልምል ፖሊሶች ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተመልምለው የመጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። ውስብስብ የምልመላ ሂደቶችን አልፋችሁ ማኅበረሰቡን ለማገልገል የፖሊስ ሙያን መርጣችሁ እና ፈቅዳችሁ ተቋሙን በመቀላቀላችሁ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።

 

ምልምል ሠልጣኝ ፖሊሶችም ሙያዊ ብቃትን የሚያሳድግ ሥልጠና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

 

ከአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ወደፊት የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ግዳጅ ተቀብለው በብቃት እንደሚፈጽሙም ተናግረዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article‎”ብቁ ወጣት” የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ ኾነ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በራይላ ኦዲንጋ ሕልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ።