
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ውስጥ ዋነኛ የቱሪዝም ምልክት ከኾኑ መስህቦች መካከል አንዱ የኾነው የጢስ ዓባይ ፏፏቴ መገኛ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶችም መመላለሻ አካባቢ ነው፤ ጢስ ዓባይ።
የጢስ ዓባይ ፏፏቴ የቱሪዝም ቱሩፋት ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከክልሉም አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍታም ድርሻው የጎላ ነው። ይሁን እንጅ አካባቢው ለቱሪዝሙ ዘርፍ ያለውን እምቅ ጸጋ እና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማይመጥን መልኩ ከአስፋልት መንገድ ተጠቃሚነት ተገልሎ ቆይቷል።
ይህ ለቱሪስቶች የእንግልት ምንጭ ኾኖ የቆየው መንገድ ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ እንዲገነባለት በመወሰኑ ታኅሣሥ 06/2012 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ እንደተቀመጠለት ይታወሳል። የባሕር ዳር – ጢስ ዓባይ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት 06/2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎም ነበር ዕቅድ የተያዘለት።
ሥራው ከአምስት ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም አሁን ላይ 50 በመቶ እንኳ መድረስ አልቻለም። ይህ ተስፋ የተጣለበት የአስፋልት መንገድ በመጓተቱ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ የመልካም አሥተዳደር ጥናቄዎችን አስነስቷል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የጭስ ዓባይ አካባቢ ነዋሪ እንደገለጹልን የመንገድ ፕሮጀክቱ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙት እንደነበር አንስተዋል። ኾኖም ግን ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ሥራዎችን ማከናወን የሚቻልበት አጋጣሚ ነበር ነው ያሉት።
የጸጥታ ችግሩ እና ሌሎች ክፍተቶችን እንደ ምክንያት ተጠቅሞ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቱን ማጓተት ግን ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።
በርካታ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለልማት ካለው ፍላጎት የተነሳ የዘራውን ሰብል እንኳ በተገቢ ሁኔታ ሳይሰበሰብ ተባብሮ እንደነበርም ጠቅሰዋል። ይህ ማኅበረሰብ ወይ በመሬቱ ወይም ደግሞ በመንገድ መሠረተ ልማቱ ተጠቃሚ አልኾነም፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ ተጓትቷል ነው ያሉት።
ሌላው የዚሁ አካባቢ ነዋሪ በሰጡን ሃሳብ መሠረት የመንገድ ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ከግማሽ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢኾንም ስድስተኛ ዓመቱን ይዟል፤ ማጠናቀቅ ግን አልተቻለም ብለዋል።
ጢስ ዓባይ አካባቢ ያለው የጸጥታ ችግር ለግንባታ ሥራው ፈተና ቢኾንም አንጻራዊ ሰላም ባለበት አካባቢ ያለውን የመንገዱን ክፍል ግን ሲሠሩ መቆየት ይችል ነበር ብለዋል። የጸጥታ ችግር በገጠመ ጊዜ የተቋረጠውን ሥራ አንጻራዊ ሰላም ሲፈጠርም በቶሎ ማስጀመር ይቻል እንደነበርም ተናግረዋል።
መንገዱ በፍጥነት ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ እና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር – ጢስ ዓባይ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ሰለሞን ወልደገብርኤል ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ትልልቅ እንቅፋቶች መግጠማቸው በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል።
የወሰን ማስከበር እና ከሦስተኛ ወገን ነጻ ማድረግ፣ የመንገድ ፕሮጀክቱን የዲዛይን ለውጥ ማድረግ፣ ለመንገድ ሙሌት የሚኾን አፈር የሚታፈስበት አካባቢ አፈር እንዳይታፈስ መከልከል፣ ለመንገድ ግንባታ ሥራው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች መዘረፍ እና የጉዳት ሰለባ መኾን፣ የሠራተኛ መፍለስ ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያቶች ነበሩ ብለዋል።
የክረምቱ የዝናብ ሁኔታ፣ ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር በአካባቢው መኖር እና በክልሉ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት የነዳጅ እና የግንባታ እቃዎችን ለማስገባት መቸገራቸውም ሌሎች እንቅፋቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።
ከ2015 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ እንደነበር የጠቀሱት ሥራ አሥኪያጁ በ2016 እና 2017 ዓ.ም ግን ሥራው ሙሉ በሙሉ የተቋረጠበት ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል። ሲያጋጥሙ በነበሩ ችግሮች ላይም ከማኅበረሰብ ወኪሎች እና ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ጋር በመወያየት ወደ ሥራ የመግባት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ጭቃ እና አቧራ እየተፈራረቀበት፣ ቤት ፈርሶበት እና በቂ ካሳ ሳይከፈለው ለልማት ሲል ተባብሯል ነው ያሉት። አሁንም ገና ካሳ ያልተከፈለው ሰው አለ፤ በማኅበረሰቡ በኩል የተነሳው ጥያቄም ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል።
አንጻራዊ ሁኔታዎችን በመጠቀም ባሕር ዳር አካባቢ ያለውን የመንገዱ ክፍል ሠርቶ ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር ነው ያሉት። ለሙሌት የሚኾን የአፈር ማፈሻ ቦታው ግን የጸጥታ ችግር ባለበት አካባቢ መኾኑ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል።
ባለፈው ሰኔ/2017 ዓ.ም ላይ በነበረው አንጻራዊ ሰላም አስፋልት የማልበስ ሥራ ላይ የደረሰውን ክፍል የማንጠፍ ሥራ ተጀምሮ እንደነበር እና በዝናቡ ምክንያት ሥራው እንደቆመም ተናግረዋል። አሁንም ላይ አስፋልት የማልበስ እንቅስቃሴውን እንደገና መጀመራቸውን እና ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ምንም አይነት የወሰን ማስከበር ጥያቄ የሌለበትን የመንገዱ ክፍል በዚህ ዓመት ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል። የወሰን ማስከበር ችግር የሚነሳባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ ችግሮች ከተፈቱም ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮችን በመገንባት ከማኅበረሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንሠራለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር ፕሮጀክት አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ዮሴፍ ወርቁ የባሕር ዳር ጢስ – ዓባይ አሥፋልት መንገድ ሥራ አሁን ላይ 48 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት።
መንገዱ 21 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ነው፤ ከዚህ ውስጥ 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩ የአፈር ቆረጣ እና ጠረጋ ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል። በመንገዱ ዳር የሚገነቡ የውኃ ማፈሰሻዎችም 45 በመቶው ተጠናቅቀዋል ነው ያሉት።
ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለመንገዱ መዘግየት አንዱ ምክንያት መኾኑን ጠቁመዋል። ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ማከነወን ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ሥራ ተቋራጩ ክፍተት ነበረበት ብለዋል። አሁን ላይ ተቋራጩ ከጸጥታው ጋር የተያያዙ ችገሮችን ቢያነሳም ሁኔታዎች ተገምግመው ወደ ሥራ እየገባን ነው ብለዋል።
መንገዱ በጥብቅ ክትትል እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ይሠራል፤ የአፈር ጠረጋ ያለቀለትን 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ እስከ ሰኔ/2018 ዓ.ም ድረስ አስፋልት ይለብሳል ብለዋል ኢንጂነር ዮሴፍ። የአስፋልት መንገድ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ቀሪ የካሳ ግምት ያልተከፈላቸውንም አርሶ አደሮች በመለየት እንዲከፈላቸው የማድረግ ተግባር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!