
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደመወዝ ጭማሪ ዋና ዓላማ የመንግሥት ሠራተኛው የኑሮ ውድነትን እንዲቋቋም ማስቻል ነው። ይሁን እንጅ በአቋራጭ ለመበልጸግ ያሰቡ ሰዎች አጋጣሚውን በመጠቀም የኑሮ ውድነትን ሲያባብሱ ይስተዋላል።
የደመወዝ ጭማሪው እንደተሰማ ያለበቂ ምክንያት የምርት መደበቅ እና ያለአግባብ በእቃዎች ላይ ዋጋ መጨመር ይስተዋላል።
መንግሥት ይህን ለመቆጣጠር እየሠራው ነው ቢልም የተዘረጋው የመቆጣጠሪያ መስመር ግን ራሱ ችግር የነበረበት ስለነበረ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ በርካቶች በኑሮ ውድነቱ እንዲቸገሩ አድርጓል።
አሁን ላይ መንግሥት በርካታ ለውጦችን ለማድረግ እየሠራቸው ካሉ ሥራዎች መካከል ሕዝብ የሚያነሳውን የአገልግሎት አሠጣጥ ለማሻሻል አንድ ርምጃ ወደፊት መስፈንጠር ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ አቅም ያለው እና የተለወጠ የሲቪል ሠርቪስ ሥርዓት መፍጠር ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ መስመር ለማዘመን የማደራጀት ሥራ እየሠራም ይገኛል።
በዚህ ማደራጀት ውስጥ ታዲያ አገልግሎት የሚሰጠው ሠራተኛ በተገቢው መንገድ ኑሮን እንዲቋቋም ለማስቻል በ2017/2018 ዓ.ም ደመወዝን ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል።
አሚኮም ልክ ከዚህ በፊት እንደነበረው ዛሬስ መንግሥት የደመወዝ ጭማሪ ሲያደርግ የንግድ ሥርዓቱ ውስጥ በአቋራጭ ለመክበር ያሰቡ ግለሰቦች የሚፈጥሩት ችግር መኖር አለመኖሩን ለመፈተሽ ገበያውን ለመቃኘት ሞክሯል።
በአንድ ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ እቃ ሲገዙ ያገኘናቸው አንጓች ፈረደ ልክ እንደዚህ ቀደሙ ባይኾንም የደመወዝ መጨመሩ ሲሰማ በእቃዎች ላይ መጨመር እየታየ ነው ብለዋል።
በርግጥ በእንዳንድ ምርቶች ላይ ቢኾንም እየታየ ያለውን አዝማሚያ መንግሥት መቆጣጠር ካልቻለ ጥሩ አይደለም ነው ያሉት።
አቶ ክንዲሁን ሞስነት እንደነገሩን የኑሮ ውድነቱ አስቸጋሪ እንደኾነባቸው እና በኑሮ ውድነት ላይ መሠራት እንዳለበት ይገልጻሉ።
አሁን ደግሞ የደመወዝ ጭማሪው እንደተሰማ በግላጭ በእቃዎች ላይ የመጨመር ነገር ባይኖርም ሰው እያዩ እቃዎች ላይ የመጨመር ነገር አለ ብለውናል መንግሥትም የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ አለበት ብለዋል።
ተዟዙረን ያነጋገርናቸው የንግዱ ማኅበረሰብ እንደሚሉት ደግሞ እቃዎች ላይ ጭማሪ የሚያደርጉት ከዕቃ ማምጫው ስለሚጨምርባቸው እንደኾነ ነው የሚናገሩት።
መንግሥት ትንንሽ ሱቆችን ብቻ ሳይኾን አከፋፋዮችንም መቆጣጠር እንደሚጠበቅበት ነው ያስረዱት።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ የደመወዝ ጭማሪ ተደረገ ተብሎ በዕቃዎች ላይ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ ባለመኾኑ ቢሮው በጉዳዩ ላይ ከጅምሩ መግለጫ ሰጥቶ ቁጥጥር እያደረገ እንደኾነ ተናግረዋል።
ቢሮው ለዋጋ ጭማሪ መሠረታዊ የሚባሉ ለምርት ማምረቻ የሚውሉ የግብዓት ዕቃዎች ጭማሪ በሌለበት፣ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ጭማሪ ባላሳዩበት እና የአውራጅ እና ጫኝ ወጭ ባልጨመረበት ኹኔታ የኑሮ ውድነትን ሊፈጥር የሚችል የዕቃ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ አግባብ እንዳልኾነ በማሳየት አስፈላጊው ቁጥጥር እስከ ቀበሌ ድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በየቀኑም የመረጃ ልውውጥ እየተደረገ እንደሚገኝ እና እንደዚ ጊዜ በቁርጠኝነት የተሠራበት ሁኔታም እንደሌለ ነው የጠቆሙት።
አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ ከምናመጣበት ጨምሯል የሚል ምክንያት መስጠቱ የተለመደ እና የተሳሳተ ማደናገሪያ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው በእያንዳንዱ ሁኔታ የገበያ ጥናት የሚደረግ በመኾኑ ማጭበርበር ፈጽሞ አይቻልም ብለዋል።
ሸማቹ እንዲህ አይነት በምርቶች ላይ ተገቢ ያልኾነ ጭማሪ እየተደረገ ካጋጠመው ጥቆማ ቢሰጥ ያለምንም ማመንታት ሕጋዊ ርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።
ሸማቹም ተሟጋች እና ለመብቱ የሚቆም መኾን አለበት የሚሉት ምክትል ኀላፊው ሁሉም እቃዎችን ተሻምቶ ከመግዛት ለምን ብሎ መጠየቅ እና መብቱን ማስከበር አለበት ነው ያሉት።
ቁጥጥሩ ባይኖር ኖሮ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ታስቦ እና ተዘጋጅቶ የነበረው ብዙ እንደነበር የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ፈንታው ፈጠነ አሁን ላይ ያለው ሥርዓት ግን ይህን አይፈቅድም ብለዋል።
ሸማቹም ከሕገ ወጥ ሥራዎች ጋር ሳይተባበር አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት ከመንግሥት ሥርዓት ማስያዝ ጋር እንዲተባበርም መክረዋል።
ንግድ ቢሮው የደመወዝ ጭማሪው እንደተሰማ በሕገ ወጥ አግባብ በሸማቹ ላይ የኑሮ ጫና ለመፍጠር በተንቀሳቀሱ እና በተጨባጭ በተረጋገጠባቸው ወደ 24 ሺህ የንግዱ ማኅበረሰብ ላይ እርምት መወሰዱንም ነው” የተናገሩት።
እርምቱ ከንግድ ሥርዓቱ ከማስወጣት እስከ ማሸግ የደረሰ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
