የሞዴል አርሶ አደሮችን ተሞክሮ በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

8

ጎንደር: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የገበሬ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከማኅበረሰቡ ከተወጣጡ አርሶ አደሮች ጋር የሰብል ልማት ሥራዎችን ምልከታ አድርጓል።

ሻምበል አዱኛው ሽገታው በጎንደር ከተማ በአትክልትና ፍራፍሬ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተዋል። አስረሳኀኝ፣ አዱኛው እና ጓደኞቻቸው በሚል ስያሜ በማኅበር ተደራጅተው ዘርፉን በመቀላቀላቸው በዓመት ጥሩ ገቢ እያገኙ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ከአትክልት እና ፍራፍሬ ባሻገርም አኩሪ አተር እያመረቱ መኾኑን ገልጸዋል።

‎ሌላው በሽንኩት ምርት የተሰማሩት አቶ መኩሪያው ዓለማየሁ ማሳቸውን በመስኖ ያለማሉ። ጠንክሮ ለሚሠራ ሰው ዘርፉ ውጤታማ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። ለአብነትም በባለፈው ዓመት ‎በበጋ መስኖ ከ30 ኩንታል በላይ ስንዴ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በሽንኩርት ምርትም 500 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ አግኝተዋል።

‎በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ለሌሎች ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውን የነገሩን አርሶ አደሮቹ በቀጣይም የተሻለ ምርት ለማግኘት የውኃ ፓንፕ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ለመስኖ ልማት ሥራው እንዲሟሉ ጠይቀዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበራ አደባ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው አርሶ አደሮች ልምድ እንዲያጋሩ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ለበጋ መስኖ ልማት የሚያስፈልግ የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ መኾኑም ተናግረዋል።

‎80 የሚደርሱ የውኃ ፓንፖችን ለአርሶ አደሮች እንዲቀርቡ መምሪያው ለክልሉ ግብርና ቢሮ ጥያቄ ማቅረቡንም አንስተዋል። በከተማ አሥተዳደሩ የሚቀረፉ ችግሮችን ለመቅረፍ በራስ አቅም እየተሠራ እንደኾነ አስረድተዋል።

‎የሞዴል አርሶ አደሮችን ተሞክሮ በማስፋት ምርታማነትን ለማሣደግ እየተሠራ መኾኑን ኀላፊው ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን አጠናክሮ ማስቀጠል ተማሪዎች ያለችግር ተምረው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል።
Next articleአምባሳደር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በጅቡቲ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኮነው ተሾሙ።