ሰላምን አጠናክሮ ማስቀጠል ተማሪዎች ያለችግር ተምረው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል።

3

ደሴ: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 ዓ.ም በሀገር እና ክልል አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ትምህርት ቤቶች የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ዕውቅና እና ሽልማት አበርክቷል።

ከፍተኛ ውጤት ያመጡት የ6ኛ፣ 8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው ከማንበብ ባለፈ ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀማቸው ለውጤት መብቃታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል። እውቅናው ሌሎች ተማሪዎችን እንደሚያነሳሳም ተሸላሚ ተማሪዎቹ ጠቁመዋል።

የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ሽልማት የተበረከተላቸው መምህራን በበኩላቸው ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ በማድረግ በተሠራ ሥራ አመርቂ ውጤት ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ክፍል ጥምርታ እና የመጽሐፍ አቅርቦት ውስንነትን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መንግሥቱ አበበ ተናግረዋል።

በሁሉም ትምህርት ቤቶች የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን በአግባቡ በመጠቀም በ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራት እና የተማሪዎችን የማሳለፍ ምጣኔ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል መምሪያ ኀላፊው።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንደሰን ልሣነወርቅ ተማሪዎች የላቀ ውጤት ያመጡት የአካባቢው ሰላም መኾኑን አንስተዋል። በዚህ ዓመትም ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የአካባቢውን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ሰልሃዲን ሰይድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወጣቶች ልማትን ማሳለጥ እና ሰላምን ማስፈን ይጠበቅባቸዋል።
Next articleየሞዴል አርሶ አደሮችን ተሞክሮ በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።